በደቡብ ሱዳን ግጭት እየተሳተፉ የሚገኙ ሁሉም ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ግጭት እንዲያቆሙና የአገሪቱ መሪዎችም በአስቸኳይ ውይይት እንዲጀምሩ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ጥሪ አቀረበ።
የአባል ሀገራት መሪዎች ይኼንኑ የደቡብ ሱዳን ግጭት አስመልክተው ዛሬ በበይነ መረብ ባደረጉት ስብሰባ መክፈቻ ላይ የተናገሩት የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ውይይቱ ከኢጋድ አባል አገራት መሪዎች መካከል በአንዳቸው ሊመቻች እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግሥት የታሰሩ ባለሥልጣናትን በፍጥነት እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል ።
ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር ጋራ ጥብቅ ግንኙነት ያለው የታጠቀ ቡድን፤ በደቡብ ሱዳን አፐር ናይል ግዛት፣ ናስር አካባቢ በሚገኝ የጦር ሠፈር ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ፣ በርካታ የምክትል ፕሬዝደንቱ አጋሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
በደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱ ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት፤ ተከትሎ ዩጋንዳ ልዩ ኃይሏን በዋና ከተማዋ ጁባ ማሰማራቷን የአገሪቱ ጦር አዛዥ ትላንት ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ/ም አስታውቀዋል ።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ፣ ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ/ም ይኼንኑ የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ያልኾኑ የመንግሥት ሠራተኞች በሙሉ ከደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ እንዲወጡ አዟል።
የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በዛሬው ስብሰባ ማጠቃለያ፣ በደቡብ ሱዳን የቀጠለውን ውጥረት በተመለከተ የጋራ መግለጫ እንደሚያወጡ ይጠበቃል ።
መድረክ / ፎረም