በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀይ መስቀል መድኃኒቶችና አቅርቦቶች በመቀሌ


ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ መቀሌ ከተማ

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ወደ ትግራይ ክልል ማድረስ የጀመረው የሕክምና ቁሳቁስ የመድኃኒት እጥረት ለማገዝ እንደሚረዳ የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ርእየ ኢሳያስ፤ በአሁኑ ግዜ በትግራይ ያለው የመድኃኒት እጥረት እንዲፈታ አሁን የተጀመረው በስፋት መቀጠል አለበት ብለዋል።

ዶ/ር ርእየ ላለፉት ስምንት ወራት መድኃኒት ወደ ክልሉ እንዳልገባና 80 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት መውደማቸውን ገልፀው አሁን ካለው ፍላጎት አንፃር እየገባ ያለው መድኃኒት በቂ አይደለም ብለዋል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የሚደረጉ በረራዎችን ወደ መቀሌ በማድረግ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለትግራይ ክልል ማድረሱን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታውቋል።

ቀይ መስቀል ዛሬ ባወጣው መግለጫም ዛሬ ባደረገው ዐስረኛው በረራ፤ ለሰዎች በጣም አስቸኳይና ሕይወት አድን የሕክምና አቅርቦቶች ማድረጉን አስታውቋል።

በጣም አስፈላጊ የሆኑ እንደ ኢንሱሊን፣ ሄሞዲያሊሲስና አስቸኳይ የሆኑ መድሃኒቶችና እቃዎችን እንዲሁም እንደ ኦክሲቶሲን፣ ቴታነስ ቶክሶይድ የመሳሰሉ መድኃኒቶችን ማድረሱን ገልጿል። በተጨማሪም ጓንትና የቀዶ ሕክምና መስጪያ መሳሪያዎችን ማቅረብ መቻሉን አስታውቋል።

በሌላ በኩል የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ፤ መቀሌ ከተማ የደረሱትን መድኃኒቶች በነዳጅ ምክኒያት ከከተማ ውጪ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማድረስ አለመቻሉን ገልፀዋል።

XS
SM
MD
LG