"ኦካምፖ ሲክስ" በሚል በአቃቤ ሕጉ ስም በዘፈቀደ የተሰየሙት እነዚህ ተጠርጣሪዎች በሰብዕና ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች ነው የክስ ዶሴ የተከፈተባቸው፡፡
ክሱ የተመሠረተባቸው በ2007 ዓ.ም በተካሄደው የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት የተነሣውን አመፅና ብጥብጥ አቀናብራችኋል፣ ወይም እጃችሁ አለበት ተብለው ነው፡፡
ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሣሾች ወደ ሄግ ችሎት የመጡት ያለአንዳች ማንገራገር ነው፡፡ ጥሪ ደረሣቸው፣ ቀረቡ፡፡ ሲጨርሱም እንደነፃ ሰዎች ወጡ፤ ወዳሻቸውም አቅጣጫ በነፃነት ይሄዳሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች በአዲሱ የኬንያ ጥምር መንግሥት ውስጥ ቁልፍ የፓርቲ ሰዎች የሚባሉት የቀድሞ የትምህርትና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሮች ዊልያም ሩቶ እና ሄንሪ ኮስጌይ እንዲሁም የራዲዮ ጋዜጠኛው ጆሽዋ ሳንግ ናቸው፡፡
የሁሉም ክስ አንድ ዓይነት ነው፤ ኬንያ ውስጥ በ2007 ዓ.ም የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አስታክኮ ለተነሣው አመፃ ተጠያቂ ናቸው የሚል ነው፡፡ በዚያ ብጥብጥ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ ሰው ተገድሏል፡፡ ቁጥራቸው ከግማሽ ሚልየን የሚልቅ ኬንያዊያን ደግሞ ተፈናቅለዋል፣ ተሰድደዋል፤ ብዙዎችም ተሣድደዋል፡፡
ያኔ ዓመፁ የተቀሰቀሰው የፕሬዚዳንት ምዋዪ ኪባኪ ደጋፊዎች ለማጭበርበር ጥረት ማድረጋቸው እንደተገለፀ ነበር፡፡ ብጥብጡ የቆመው ታዲያ ፕሬዚዳንት ኪባኪና ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ጥምር መንግሥት ሊመሠርቱ ስምምነት ከመፈረሙ በኋላ ነበር፡፡
የዛሬው ችሎት የተሰየመው ተከሣሾቹ መብቶቻቸውን ማወቃቸውንና የቀረበባቸውንም ክስ በትክክል መረዳታቸውን ለማረጋገጥ ነበር፡፡ ሁሉም ተከሣሾች ሁሉም ነገር ግልፅ እንደሆነላቸው ተናግረዋል፡፡
ነገ፣ (ዐርብ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ ሌሎች ሦስት የኬንያ ፖለቲከኞች ለተመሣሣይ ጉዳይ ሄግ ዳኞች ፊት ይቀርባሉ፡፡
ጉዳዩ ለፊታችን ነኀሴ 26 ተቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ግን “ጉዳዩን እዚሁ እቤቴ ውስጥ አየዋለሁ” ሲል የኬንያ መንግሥት ዓለምአቀፉ የወንጀል ችሎት ከፍርዱ ሂደት እንዲወጣ የጥያቄ ደብዳቤ ፅፏል፡፡ ይህንንም አቤቱታ ዳኞቹ እያዩት ስለሆነ “ውሣኔ ይሰጡበታል” ተብሏል፡፡