በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል ከ700 በላይ ሰዎች በረኀብ እንደሞቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ


በትግራይ ክልል ከ700 በላይ ሰዎች በረኀብ እንደሞቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:40 0:00

ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የምግብ ርዳታ ሥርጭት ማቋረጣቸውን ተከትሎ፣ በትግራይ ክልል በቅርብ ሳምንታት ውስጥ፣ ከ700 በላይ ሰዎች በረኀብ እንደሞቱ፣ የክልሉ ባለሥልጣናት እና ተመራማሪዎች መናገራቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ሁለቱ ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላት፣ በትግራይ ክልል ለተቸገሩ ሰዎች የሚላከው የስንዴ ርዳታ ተሰርቆ ለገበያ እንደቀረበ ከተደረሰበት በኋላ፣ ባለፈው መጋቢት ወር፣ ለክልሉ የሚሰጡትን የምግብ ርዳታ አቋርጠዋል፡፡ ከዚያም በማስከተል፣ በዚኽ ሰኔ ወር፣ 20 ሚሊዮን ሰዎች ወይም ከጠቅላላው ሕዝቧ አንድ ስድስተኛው፣ የምግብ ችግር ላይ ላለባት ኢትዮጵያ የሚሰጡትን የምግብ ርዳታ በጠቅላላው አቋርጠዋል፡፡

የትግራይ ክልል የአደጋ ዝግጁነት ኮሚሽን፣ የምግብ ርዳታው ከተቋረጠ ወዲህ፣ ከክልሉ ሰባት ዞኖች በሦስቱ፣ 728 ሰዎች ከረኀብ ጋራ በተያያዘ ምክንያት እንደሞቱ መዝግቧል፡፡ ኮሚሽኑ አኀዛዊ መረጃውን ያሰባሰበው፣ በየወረዳው ከሚገኙ ባለሥልጣናት እንደኾነ፣ ሓላፊው አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም፣ “በትግራይ ባለው በጣም አስቸጋሪ ኹኔታ፣ ብዙ ሰዎች በምግብ ዕጦት እየሞቱ ነው፤” ማለታቸውን፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ በዘገባው ጠቅሷል፡፡

በረኀብ ከሞቱት ከ728ቱ ውስጥ 350ዎቹ፣ በክልሉ ለሁለት ዓመታት በተካሔደው ጦርነት ምክንያት፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከተጠለሉበት ሰሜን ምዕራባዊ ዞን እንደኾኑ፣ ዘገባው አመልክቷል፡፡ እ.አ.አ መጋቢት አጋማሽ ላይ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የተራድኦ ድርጅት ባለሥልጣናት፣ የዞኑ ትልቋ ከተማ በኾነችው ሽሬ በሚገኝ ገበያ፣ ለ134 ሺሕ ሰዎች የሚበቃ የምግብ ርዳታ ሲሸጥ ማግኘታቸውን ዘገባው አውስቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ በክልሉ የምግብ ርዳታው መቋረጡን ተከትሎ፣ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው ሰባት ካምፖች፣ 165 ሰዎች በረኀብ እንደሞቱ መዝግበዋል፡፡ በክልሉ ውስጥ፣ ከ100 በላይ ተመሳሳይ መጠለያ ጣቢያዎች አሉ።

በጦርነቱ ምክንያት ስለተፈናቀሉት ሰዎች የሚያጠኑት ተመራማሪዎቹ፣ የሟቾቹን አኀዝ ያሰባሰቡት፣ ከተፈናቃዮቹ የመጠለያ ካምፖች አስተባባሪዎች ነው፡፡ “የበቀል ጥቃት ይደርስብኛል” በሚል ስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንደኛው ተመራማሪ ተጠይቀው እንደገለጹት፣ ከሞቱት መካከል የሚበዙት፥ ሕፃናት፣ በዕድሜ የገፉ እና የልዩ ልዩ በሽታዎች ተጠቂዎች እንደኾኑ አመልክተዋል፡፡ የሰዎቹ ኅልፈት ምክንያትም፣ በቀጥታ ከምግብ ርዳታው መቋረጥ ጋራ የተያያዘ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ዘገባው አያይዞም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ ሰኔ 14 ባወጣው ሪፖርት፣ እ.አ.አ ካለፈው 2022 ሚያዝያ ወር እስከ ዘንድሮ 2023 ሚያዝያ ወር በነበረው ጊዜ፣ በክልሉ ውስጥ፣ በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት የተነሳ ታምመው ሆስፒታል የገቡ ሕፃናት ቁጥር፣ በ196 ከመቶ እንዳሻቀበ ጠቁሟል፡፡

ለሁለት ዓመታት የተካሔደው ጦርነት፣ በትግራይ ከሚኖረው ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ፣ 4ነጥብ5 ሚሊዮኑን የምግብ ርዳታ ጠባቂ አድርጓል፡፡ በጦርነቱ ወቅት፣ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች፣ የሰብአዊ ርዳታ ዘረፋ እንደፈጸሙ ሲገለጽ፣ የአገሪቱ መንግሥት፣ የተራድኦ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በመገደቡ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪዎች፣ “መንግሥት፥ ረኀብን በጦርነት መሣሪያነት እየተጠቀመ ነው፤” በማለት መወንጀላቸው ይታወሳል፡፡ ባለፈው ኅዳር ወር፣ ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ማክተሙን ተከትሎ፣ ለክልሉ የሚደርሰው ርዳታ እንዲቀጥል ተደርጎ ነበር፡፡

የምግብ ርዳታ ስርቆቱን በተመለከተ፣ በቀዳሚነት መዘገቡን ያስታወሰው አሶሺዬትድ ፕረስ፣ አድራጎቱ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጥልቅ እንደተሳተፉበት፣ የረድኤት ሠራተኞች እንደነገሩት ጠቅሷል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ባለሥልጣናቱ ከርዳታ ማከፋፈል ሒደቱ ካልተገለሉና ጠንካራ የቁጥጥር ርምጃ ካልተወሰደ፣ ሥርጭቱን እንደማትቀጥል አስታውቃለች፡፡

በትግራይ እና በሌሎችም ክልሎች፣ ለምግብ ርዳታው መሰረቅ ዋና ተጠያቂው መንግሥት ነው፤ መባሉን፣ “ጎጂ ፕሮፓጋንዳ” ሲል አጣጥሎ፣ ኾኖም፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ በመተባበር ምርመራ ለማካሔድ ተስማምቷል፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በበኩሉ፣ የራሱን ምርመራ በማካሔድ ላይ ይገኛል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በኢትዮጵያ የምግብ ርዳታ ሥርጭታቸውን ቢያቋርጡም፣ ለሴቶች እና ለሕፃናት የሚያደርጉትን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት መርሐ ግብር ግን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ ይኹንና፣ ርዳታው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሲሰናከል መቆየቱን፣ የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ አክሎ ገልጿል፡፡

XS
SM
MD
LG