የቱኒዝያ ፕሬዚዳንት ኬይስ ሰይድ “ሕገ ወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር” በሚል የአፍሪካ ኅብረት “ዘርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ንግግር” ሲል የጠራውን ንግግር ካሰሙ አስር ቀን በኋላ፣ በትናንት እሁድ ንግግራቸው ዘረኝነትን አውግዘዋል፡፡ ይህን የሚፈጽሙትም በሕግ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ በትናንቱ ንግግራቸው የስደተኞችን ፍልሰት “የቱኒዝያን የሕዝብ ስብጥር ብዙ አፍሪካዊ ጥቂት አረብ እንዲሆን ለማድረግ የተዘየደ ሴራ ነው ሲሉ የተናገሩትን ደግመውታል፡፡
አገሪቱን በዘረኝነት መክሰስም “ምንጩ ከየት እንደሆነ ይታወቃል” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡ የምንጩንና ሴራው ባለቤት ግን ማን እንደሆነ አላብራሩም፡፡
ፕሬዚዳንቱ የካቲት 14/2015 ባሰሙት ንግግራቸው የደህንነት ኃይሎች ሁሉንም ህገ ወጥ ስደተኞች ከአገር እንዲያባርሩ አዘዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ ተከትሎ ፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞችን ያሰረ ሲሆን፣ የቤት አከራዮችም በመቶዎች የሚቆጠሩትን ከየቤታቸው ሲያስወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞችም ከየሥራ ገበታቸው መባረራቸውን የመብት ተሟጋቾች አስታውቀዋል፡፡
ብዙ ስደተኞች በወሮበሎች ቡድን በድንጋይ መወገርን ጨምሮ ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን የመብቶች ተሟጋቾች በሪፖርቶቻቸው ጠቁመዋል።
ፕሬዚዳንቱ ስለ ስደተኞች ካሰሙት የምሬት ንግግር በኋላ የተቀሰቀሰውን የአመጽ ጥቃት በመፍራት ባላፈው ቅዳሜ ወደ 300 የሚደርሱ ሰዎች ቱኒዚያን ለቀው ወደ ማሊ እና አይቮሪኮስት መመለሳቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የማሊ የመከላከያ ሚኒስቴር ሳዲዮ ካማራ ድርጊቱን ያወገዙ ሲሆን “ወገኖቻችን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል፡፡ እነዚህ የቱኒዝያን ባለሥልጣናትም ሆነ ሕዝብ የማያስከብሩ ድርጊቶችን ስናወግዝ እያዘንን ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ከሰሃራ በታች ያሉ ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮችም በሁኔታው በመደናገጥና በመፍራት ወደ የኤምባሲዎቻቸው እየጎረፉ ያሉ ዜጎቻቸውን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተራኮቱ መሆኑን ተዘግቧል፡
የአፍሪካ ኅብረትም ድርጊቱ እጅግ ያስደነገጠውና ያሳሰበው መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
የቱኒዝያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመብቶች ተሟጋች ቡድኖች ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እስር ጋር የተገጣጠመው የፕሬዚዳንት ኬይስ ሰይድ የህገ ወጥ ስደተኞች እስር ዘመቻ ትኩረቱን በቱኒዝያ ከገጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር አቅጣጫ ለማስቀየር የተደረገ ነው ብለውታል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡