በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሂዩማን ራይትስ ዋች ከፍተኛ አጥኝ ስለኢትዮጵያ ሪፖርቱ ተናገሩ


ሂዩማን ራይትስ ዋች በቅርቡ የኢትዮጵያን መንግሥት ከእርዳታ ጋር በተያያዘ በአፈና ተግባር የከሰሰበትን ሪፖርት ወደማውጣት የወሰደውን ምክንያት የድርጅቱ የአፍሪቃ ፕሮግራም ከፍተኛ የጥናት ኃላፊ ሌስሊ ሌፍኮው ሲናገሩ “የኢትዮጵያ መንግሥት ለብዙ ጊዜ እርዳታን ለፖለቲካ ጭቆና ይጠቀማል ተብሎ ሲከሰስ ቆይቷል፤ ጥናቱንም ለማካሄድ ያነሳሳን ይህ እውነት መሆኑን ለማወቅ ነው። እውነት ከሆነስ በአገሪቱ የተንሰራፋ ነው ወይስ በአንድ አካባቢ የተወሰነ? ብለን ነበር፡፡ የሚያሣዝነው ግን ከገመትነው በላይ በብዙ አካባቢዎች ተስፋፍቶ የሚሠራበት ሆኖ ማግኘታችን ነው።” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ተቃውሞን ለማፈን ከለጋሾች የሚሰጠውን እርዳታ እንደመሣሪያ ይጠቀማል ሲል ዓለምአቀፍ የስብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች ባለፈው ሣምንት መባቻ “Development without Freedom: How Aid Underwrites Repression in Ethiopia” “ልማት ያለ ነጻነት፤ በኢትዮጵያ እርዳታ እንዴት ለጭቆና እንደሚውል” በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት መክሰሱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሪፖርቱ “የመንግሥትን ስም የማጉደፍ ዓላማ አለው” ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል።

ለኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚሰጡ መንግሥታትና ድርጅቶች ተወካዮች ሪፖርቱ በጥልቁ እንደሚያሳስባቸው ገልፀው በእርዳታ እደላ ላይ ችግር አይኖርም ብሎ ማስተባበል ባይቻልም ሆን ተብሎ ለፖለቲካ ጭቆና ግል አይውልም ብለዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች በኢትዮጵያ ላይ ስላወጣው ሪፖርት ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንዲሰጡ ትዝታ በላቸው የድርጅቱን የአፍሪቃ ፕሮግራም ከፍተኛ የጥናት ሃላፊ ሌስሊ ሌፍኮውን አነጋግራለች፡፡

ዓለም አቀፉ የስብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች በዚህ ሪፓርቱ በኢትዮጵያ ገጠሮች የሚኖሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ብዙ ጊዜ ብድር፣ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የምግብ እርዳታና የመጠለያ ድጋፍ ይከለከላሉ ሲል ነው የኢትዮጵያን መንግሥት የሚከስሰው።

ሌስሊ ሌፍኮው ድርጅታቸው እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጥናቱን እንዴት እንዳካሄደ ሲያስረዱ “የኢትዮጵያ መንግሥት ለብዙ ጊዜ እርዳታን ለፖለቲካ ጭቆና ይጠቀማል ተብሎ ሲከሰስ ቆይቷል፤ ጥናቱንም ለማካሄድ ያነሳሳን ይህ እውነት መሆኑን ለማወቅ ነው። እውነት ከሆነስ በአገሪቱ የተንሰራፋ ነዉ ወይስ በአንድ አካባቢ የተወሰነ? ብለን ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከገመትነው በላይ በብዙ አካባቢዎች ተስፋፍቶ የሚሠራበት ሆኖ ማግኘታችን ነው።” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩኒኬሽንስ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን “ሂዩማን ራይትስ ዋች እንደፈለገው ባለፈው ምርጫ ተቃዋሚዎች ሥልጣን ስላልያዙ ተስፋ ቆርጦ የመንግሥትን ስም ለማጉደፍ ያቀደው ነው፡፡” ብለዋል ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ የእንግሊዘኛው ቋንቋ ሥርጭት በሰጡት መልስ። “ዘገባው አይታመንም፤ ሂዩማን ራይትስ ዋችም በኢትዮጵያ መሠረት የለውም፡፡” ብለዋል አቶ በረከት ስምኦን፤

የሂዩማን ራይትስ ዋችዋ የአፍሪካ ፕሮግራዋ ዋና አጥኚ ግን “ይህ አዲስ ነገር አይደለም - ይላሉ

- ብዙውን ጊዜ ጨቋኝ መንግሥታት የሪፖርታችንን ይዘት አይቀበሉም፣ በጣም የምያሣዝን ነዉ፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ችግር በመሆኑ መንግሥት ይህን ተቀብሎ የራሱን ምርመራ ያደርጋል፣ ችግሩንም ይፈታል የሚል ነው የኛ ተስፋ።”

ዓለም አቀፉ የመብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ የሚሰጠውን እርዳታ ለፖለቲካ ጭቆና ያውላል በማለት ባወጣው ሪፖርት ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት USAID እና የካናዳው ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት CIDA ባወጧቸው መግለጫዎች ሪፓርቱ በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል። “በኢትዮጵያ በእርዳታ እደላ ላይ ችግር የለም ለማለት ባይቻልም ችግሩ በአሠራር ደረጃ ወይም ሆን ተብሎ በተቀናጀና በመንግሥት መመሪያ የሚካሄድ አይደለም” ብለዋል። ካሁን በፊት ተመሣሣይ ክስ ተነስቶ እንደነበርና ምርመራ ተካሄዶ ያገኙት ጭብጥ ከድርጅቱ ድምዳሜ የተለየ መሆኑንም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የሚገኘው Development Assistant Group (የልማት እርዳታ ቡድን) 24 ለጋሽ አገሮችና ድርጅቶችን አስተባብሮ የሚመራው የልማትና የተራድዖ ቡድን በግሉ ያካሄደው ጥናት፣ ሂዩማን ራይትስ ዋች ደረስኩበት ካለው ድምዳሜ ጋር እንደማይጣጣም በመጥቀስ መግለጫ አዉጥቷል፥ የድርጅቱ ፕሮግራም አቀናባሪ ቪክቶሪያ ቺሣላ እንዲያነጋግሩን ጠይቀን ፈቃደኛ አልሆኑም። ሆኖም የልማት እርዳታ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ ላይ መልስ እንዳላቸው የሂዩማን ራይትስ ዋችዋን ሌስሊ ሌፍኮውን ጠይቀናል።

በቡድኑ የታቀፉት ድርጅቶች “ከቢሯቸው ጠረጴዛ ስላካሄዱት ጥናት ነው የሚናገሩት፤ ወደ ኢትዮጵያ ገጠሮች ሰው ልከው አራሾችን አነጋግረው ያጠናቀሩት ጥናት አይደለም። የሚጠቀሙበት የእርዳታ አስጣጥ ቁጥጥር ሥርዓት በትክክል ይሥራ አይሥራ የገመገሙበት ነው። እሱም ቢሆን፣ የእርዳታ አስጣጥ ሥርዓቱ ከፍተኛ ድክመት እንዳለው ነው የጠቆማቸው፡፡ መሻሻል የሚያስፍልጋቸው ብዙ ክፍተቶች እንዳሉት ጥናቱ በእርዳታ አሰጣጥ ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንና ወደፊት ግን ጠለቅ ያለ ምርመራ እንደሚያስፈልግ ነው ውጤቱ የጠቆመው። ሆኖም ግን ይህ ውጤት በእጃቸው እያለ የኛን ጥናት ውጤት መቃወማቸው ያስገርማል።” ብለዋል፡፡

ሚስ ሌፍኮው አክለውም “እንዲህ ዓይነቱን የእርዳታ እህል ለፖለቲካ ተቃዋሚ መቅጫ መጠቀም ክልልም ባይሆን በጣም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለባት አዲስ አበባና በሦስት ክልሎች፣ ማለትም በኦሮሚያ፣ በአማራና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ላይም ሪፖርት ማድረጋችን፣ በጣም ሰፊ በሆነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ከሃምሣ በላይ በሚሆኑ ቀበሌዎች ማየታችን የችግሩን ስፋትና ተደጋጋሚነት ያሳያል። እኛ እንዲሁ ክልል ላይ አምባገንን የሆኑ ግለስቦች በግላቸው ተነሳስተው የሚፈጽሙት ወንጀል አይመስለንም፤ ተያያዥነት አለዉ” ብለዋል፡፡ ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG