የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታና አጠቃላይ አስተዳድር ከዩናይትድ ስቴይትስ ፖሊሲ ጋር ለመቃነት ያለመው ውሳኔ 128 በዩናይትድ ስቴይትስ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ፊት ቀርቦ ያለምንም ተቃውሞ ጸድቋል።
ውሳኔ 128 “በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ክብር የቆመ ሁሉን አቀፍ አስተዳድር እንዲሮን ለመደገፍ” ይላል በመቅድሙ።
በዴሞክራቶችና ሪፐብሊካን አባላት ድጋፍ የጸደቀው ውሳኔ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የሚታዩ ያላቸውን የመብት ጥሰቶችና የዴሞክራሪያ አስተዳድር በደሎች የዘርዘረና፤ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የደረሱ ግድያወችን የሚያወግዝ ነው። ህጉን ያረቀቁት የኒውጀርሲው ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት ውሳኔው ለድምጽ ሲቀርብ ባሰሙት ንግግር “ኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥና የምጣኔ ሀብት ተሳትፎ እድል በጠየቁ ወጣቶች” በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልል ለረጂም ጊዜ የዘለቁ ሰልፎች እንደተካሄዱባት አስታውሰው፤ መንግስቱ ግን “ከልክ ያለፈ ሃይል” በመጠቀም ከ1ሽህ በላይ ዜጎቹን ገድሏል ሲሉ ለኮንግረሱ አባላት አስረድተዋል።
በዛሬውለት የኦክሎሃማው ሴናተር ጄምስ ኢንሆፍ በዋሽንግተን የፖለቲካ ክበቦች በሚነበበው ዘ-ሒል ላይ ባሳተሙት ጽሁድ፤ ውሳኔ 128ን የምክር ቤቱ አባላት ውድቅ እንዲያደርጉት ጠይቀው ነበር። ለዚህም የሰጡት ምክንያት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አቢይ አሕመድና አስተዳድራቸው ለውጥ እንዲያመጡ እድል እንስጥ የሚል ነበር።
የኒውጀርሲው ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት ማምሻውን ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የሚመጡ የአመራር ለውጦች በተለምዶ ብዙ ቃል የሚገባባቸውና “የተገቡት ቃላት ግን የማይሟሉባቸው ናቸው” ብለዋል።
በአዳራሹ ዙሪያ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን በውሳኔ 128 መጽደቅ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ