በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በእሥራዔል እርዳታ ጉዳይ አሜሪካ ተፋጥጣለች


አፈጉባዔ ማይክ ጆንሰን
አፈጉባዔ ማይክ ጆንሰን

ለእሥራዔል የ14 ቢሊዮን ተኩል ዶላር (ወደ 780 ቢሊዮን ብር) እርዳታ ለመላክ በተያዘው ዕቅድ ላይ በተወካዮች ምክር ቤቱ ሪፓብሊካን እንደራሴዎች በአንድ በኩል፤ በሌላ ደግሞ በዴሞክራቲክ ፓርቲው የበላይነት በተያዘው የህግ መወሰኛ ምክር ቤትና በዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት መካከል የከረረ መፋጠጥ መፈጠሩን ሮይተርስ ዘገበ።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቀደም ሲል ያስገቡት ለእሥራዔል፣ ለዩክሬንና ለታይዋን፣ እንዲሁም ለሰብዓዊ እርዳታ ጉዳዮች ይውላል ያሉት የ106 ቢሊዮን ዶላር (ወደ 6 ትሪልዮን ብር) ጥቅል ጥያቄ ቢሆንም ሪፓብሊካኑ እንደራሴዎች ግን የእሥራዔል ድርሻ ከሃገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤቱ በጀት ላይ ተቆርጦ እንዲሰጥ የሚጠይቅ የህግ ረቂቅ ባለፈው ሰኞ ይፋ አድርገዋል።

ይህ ጉዳይ በአዲሱ ሪፓብሊካን አፈጉባዔ ማይክ ጆንሰን እየተመራ ላለው ምክር ቤት የመጀመሪያው ፈተና መሆኑን ሮይተርስ አክሎ ጠቁሟል።

የሃገሪቱ የብር ቦርሣ ባለቤት ነው በሚባለው ህግ መምሪያ ሪፓብሊካኑ 221 ለ212 በሆነ ልዩነት አብላጫውን የያዙ ሲሆን በህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ውስጥ ግን ዴሞክራቶቹ 51 ለ49 በሆነ መቀመጫ የበላይነቱን ተቆጣጥረዋል።

ዛሬ ምሽት ላይ በህግ መምሪያው ድምፅ ይሰጥበታል የተባለው የሪፓብሊካኑ ረቂቅ ቢፀድቅ እንኳ የፕሬዚዳንቱን ሙሉ ጥቅል ሳያካትት ተቀነጣጥቦ ለህግ መወሰኛው ቢላክለት “ሙት ሆኖ እንደሚደርስ” የሴኔቱ ዴሞክራቲክ አብዝኃ መሪ ቸክ ሹመር አስጠንቅቀዋል።

በዚያ ላይ የሃገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤቱን በጀት የመነካካቱ ጉዳይ የግብርና ቀረት አሰባሰቡን ሥራ ይጎዳል በሚሉት ዴሞክራቲክ እንደራሴዎች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው እየተሰማ ነው።

ለዩክሬን የሚላክን እርዳታ በሚመለከት ምንም እንኳ ዴሞክራቶቹና የሚበዙት ሪፓብሊካን ድጋፍ ያላቸው ቢሆንም ‘ዩናይትድ ስቴትስ የጠለቀ የበጀት ክፍተት እየተጋፈጠች ነው’ የሚሉ ጥቂት፣ ግን ድምፃቸው ጎልቶ የሚሰማ ሪፓብሊካን በዚህ ወቅት እርዳታውን የመቀጠሉን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ሲያስገቡ ይሰማሉ።

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጫረ ከየካቲት 2014 ዓ.ም. አንስቶ ኮንግረሱ ለዩክሬን የ113 ቢሊዮን ዶላር (6 ትሪልዮን ከሩብ ብር) ድጋፍ አፅድቋል።

ለእሥራዔል የታሰበው እርዳታ ከባይደን ጥቅል ተነጥሎ ወጥቶ ቢቀርብና የሃገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤቱ በጀት ቢቆረጥ ሃገሪቱ አሁን ባለባት የ1.7 ትሪልዮን ዶላር የበጀት ክፍተት ላይ 30 ቢልዮን ዶላር እንደሚያክልበት የየትኛውም ፓርቲ ወገን ያልሆነው የተወካዮች ምክር ቤቱ የበጀት ቢሮ አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG