በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአንጋፋዋ ድምፃዊት እና ዘማሪት ኂሩት በቀለ ስንበት


የአንጋፋዋ ድምፃዊት እና ዘማሪት ኂሩት በቀለ ስንበት
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:00 0:00

አንጋፋዋ ድምፃዊት ኂሩት በቀለ፣ በአደረባት ሕመም፣ በ83 ዓመቷ፣ ከዚኽ ዓለም በሞት ተለይታለች። በዘመናዊ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ፣ ከግንባር ቀደም እንስት ድምፃውያን ተርታ የምትመደበው፣ የቀድሞዋ ሙዚቀኛ እና በኋላም በዘማሪነት ያገለገለችው ተወዳጇ ኂሩት በቀለ፣ በዐዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና በሚባለው አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ፣ ዛሬ ዐርብ፣ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ማለዳ ማረፏ ተሰምቷል።

አንጋፋዋ ዜመኛ ኂሩት በቀለ፣ ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባችው ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ ሲኾን፣ በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ራዲዮ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፣ የመጀመሪያ ሥራዋ “የሐር ሸረሪት” የሚል እንደነበር ተናግራለች። ኂሩት በዚኽ ቃለ መጠይቋ ላይ፣ ሲሳይ የተባለ ወታደር ጎረቤታቸው፣ የድምጿን ማማር ተመልክቶ ወደ ሙዚቃው እንድታዘንበል እንደገፋፋት አውስታለች፡፡ ከዚኽም ጋራ፣ ከጨቅላ ዕድሜዋ አንሥቶ ለትምህርት ቤት ጓደኞቿ በመዝፈን ያገኘችው ማበረታቻና በልጅነቷ፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሙዚቃ ዝግጅቶችን መታደሟ፣ ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመግባት እንዳነሣሣት አስረድታለች፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድራ ባለፈችበት የምድር ጦር ኦርኬስትራ፣ በ60 ብር ተቀጥራ ሥራ ስትጀምር፣ ቤተሰቦቿ መረጃው አልነበራቸውም፡፡ በቆይታም፣ ልጃቸው ሙዚቀኛ እንደኾነች በብሔራዊ ቲያትር ቤት በሥራ ላይ ሳለች የተመለከቱት ቤተሰቦቿ፣ በቅድሚያ ኀዘን ቢሰማቸውም ከጊዜ በኋላ ሞያዋን አምነው እንደተቀበሉት ተናግራለች።

በተለይ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ያበቡት ዘመናዊ የሙዚቃ ቡድኖች፣ አጉልተው ካወጧቸው ጥቂት ዕንቁ ድምፃውያን ውስጥ፣ ኂሩት በቀለ ተጠቃሿ ነበረች። በእኒያ ሁለት ዐሥርት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዓመታት፥ የክብር ዘበኛ፣ የምድር ጦር እና የፖሊስ ሠራዊት፣ በተባሉ የሙዚቃ ቡድኖች መካከል የነበረውን ጠንካራ ፉክክር፣ በጊዜው የነበሩ የሙዚቃ አድናቂዎች ሁሉ ያስታውሱታል።
ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አሕመድ እና ብዙነሽ በቀለ ከክብር ዘበኛ፤ ኂሩት በቀለ፣ ዓለማየሁ እሸቴ እና ሙሉ ቀን መለሰ ከፖሊስ ሠራዊት፤ ታምራት ሞላ እና ሌሎችም ደግሞ ከምድር ጦር ኦኬስትራ የፉክክሩ ድምቀቶች ነበሩ።

በዚያ ፉክክር እና ውድድር መካከል፣ ከምድር ጦር ኦኬስትራ ወደ ፖሊስ ሠራዊት የተዘዋወረችው ኂሩት በቀለ፣ ኮከብ ድምፃዊት ኾና እመርታዋን አሐዱ ብላለች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ መንፈሳዊ የዝማሬ አገልግሎት እስከገባችበት የ1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ፣ ዘመን ተሻጋሪ በኾነ የሞያ ብቃት እና ተሰጥኦ፣ አድናቂዎቿንና አገሯን አገልግላለች።

የኂሩት በቀለ አብዛኞቹ ሥራዎች፣ ዘመን ተሻጋሪ እና ለበርካታ ሴት ድምፃውያን ማሟሻ የኾኑ ናቸው። የዜማ ድርሰቶችንም ትደርስ የነበረ ሲኾን፣ ከመሐሙድ አሕመድ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ መልካሙ ተበጀ እና ሌሎችም አንጋፋ ድምፃውያን ጋራም ሥራዎቿን ለሕዝብ አቅርባለች፡፡

በበርካታ ድምፃውያን ከሚያቀነቀኑት የፍቅር ዜማዎች በተጨማሪ፣ ዛሬም ድረስ በአድናቆት የሚደመጡ፣ ሀገረ ኢትዮጵያንና ብሔራዊ ስሜትን የተመለከቱ ሙዚቃዎችንም ተጫውታለች። ለአብነትም፣ “ደጋ ወይና ደጋ” እና “ኢትዮጵያ” የሚሉት ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች፣ ከትላንት እስከ ዛሬ እንደተወደዱ ዘልቀዋል።

ጥዑመ ዜማ ኂሩት በቀለ፣ ለ35 ዓመታት ያህል፣ በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ እና የቴአትር ክፍል ውስጥ አገልግላለች። በእነዚኽ ዓመታት ውስጥም፣ “ሕይወት እንደ ሸክላ”ን ጨምሮ ከ200 በላይ ድንቅ ሙዚቃዎችን ከዋልያስ፣ ከሮሃ እና ከዳህላክ ባንዶች ጋራ ስትጫወት፣ ከእነርሱም 38 የሚኾኑቱ በሸክላ ታትመዋል፤ እያንዳንዳቸው 10 ዜማዎችን የያዙ 14 ካሴቶችም ለኅትመት መብቃታቸውን፣ ዜና ሕይወቷ ያስረዳል።

አንጋፋዋ ድምፃዊት ኂሩት በቀለ፣ ወደ ኋለኛ ዘመኗ፣ ከ1952 እስከ 1987 ዓ.ም. ድረስ ከቆየችበት የሙዚቃዋ ሞያዋ ራሷን ማግለሏን በማስታወቅ፣ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት እና የዘማሪነት አገልግሎት አዙራለች።

ከአባቷ የመቶ አለቃ በቀለ ክንፌ እና ከእናቷ ተናኘ ወርቅ መኮንን፣ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. በዐዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና አካባቢ የተወለደችው አንጋፋ ድምፃዊት እና ዘማሪት ኂሩት በቀለ፣ በአደረባት ሕመም በሀገር ውስጥ እና በውጭ በሕክምና ስትረዳ ቆይታ በተወለደች በ83 ዓመቷ ነው ያረፈችው፡፡ የሰባት ልጆች እናት፣ የ10 ልጆች አያት እና የሰባት ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።

XS
SM
MD
LG