ሃሪኬን ሣንዲ ተብሎ የተጠራው ይህ ሰፊ የውቅያኖስ ማዕበል ከሃምሣ ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ዓይነቱ ያልታየ ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲን እና ግዙፏን የዓለም የንግድ ማዕከል ኒው ዮርክን ጨምሮ እጅግ በርካት ከተሞች ዝግ ናቸው፡፡
የአየር በረራዎችና የባቡር መሥመሮችን ጨምሮ በክልሉ ውስጥ ያሉ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፡፡ ማዕበል ሣንዲ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የአትላንቲክ የጠረፍ አካባቢዎች እየተቃረበ በመጣ ቁጥር የንፋሱ ፍጥነት በሰዓት ወደ 150 ኪሎሜትር መድረሱ ታውቋል፡፡
ዘጠኝ ስቴቶችና ዋሽንግተን ዲሲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥተዋል፡፡
በማዕበሉ ምክንያት የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሰኞ ዝግ ሆነዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማም የማዕበሉን እንቅስቃሴ፣ ሰዎችን የማዳንና ፈጣን እርምጃ የመውሰዱን ሥራ በቅርብ ለመከታተልና ከዋይት ኃውስ በመምራት ላይ ለማተኮር የነገ ሣምንት ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይዘውት የነበረውን የምረጡኝ ዘመቻ አቋርጠዋል፡፡
ተቀናቃኛቸው የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ሚት ራምኒም እንዲሁ አንዳንድ የዘመቻ እንቅስቃሴዎቻቸውን ለማቋረጥ ተገድደዋል፡፡
ሃሪኬን ሣንዲ በካሪቢያን አካባቢ ባለፈችባቸው መንገዶቿ ላይ ቢያንስ 65 ሰዎችን መግደሏ እስከአሁን ተዘግቧል፡፡
ዝርዝሩን ከዘገባው ያዳምጡ