በኢትዮጵያ ሐረሪ ክልል፣ በየዓመቱ የሚከበረውን ሸዋሊድ በዓልን በቅርስነት የማስመዝገብ ዕድል መኖሩ ተጠቆመ። በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀ የጥናት ውይይት ላይ፣ በመጪው ኅዳር ወር በማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ በቅርስነት ሊመዘገብ እንደሚችልም ተመልክቷል።
“ሸዋሊድ”፥ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ የወርኀ ረመዳን ጾም ከተጠናቀቀ በኋላ፤ የእምነቱ ተከታዮች እንደፍላጎታቸው በተጨማሪ የሚጾሟቸው ስድስት የወርኀ ሸዋል ቀናት ሲጠናቀቁ የሚከበር በዓል ነው። በኢትዮጵያ ይህ በዓል የሚከበረው፣ በሐረሪ ክልል በሐረር ከተማ ውስጥ ነው።
ትላንት ኀሙስ፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከበረው በዚኽ በዓል ላይ በተዘጋጀ ዐውደ ጥናት፣ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ሓላፊ ኤልያስ ሽኩር፤ በዓሉ በመጪው ኅዳር ወር ከኢትዮጵያ የማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ቅርሶች አምስተኛው ኾኖ ሊመዘገብ እንደሚችል ተናግረዋል።
“ሸዋሊድ” ሃይማኖታዊ መነሻ እንዳለው በክልሉ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል። ያም ኾኖ አከባበሩ ባህላዊ እንደኾነ ይስረዳሉ። በባህላዊ ልብስ አጊጦ በባህላዊ ጭፈራ የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው። ከዚኽ ቀደም፣ የሐረሪ ሴቶች ባላቸው አልባሳት እና መዋቢያዎች አጊጠው በአደባባይ ሲጫወቱ የሚውሉበት ብቸኛ ቀን ስለነበር፣ ወንዶች ሴቶችን በግላጭ የሚያዩበት ብቸኛ አጋጣሚ እንደነበር ተሳታፊዎች አውስተዋል። በዚኽም ምክንያት በዓሉ እንደ መተጫጫ ይቆጠርም ነበር፤ ይላሉ።
ሴቶች፣ እንደቀደሙት ዘመናት ቤት የሚውሉ ባለመኾናቸውና ዘመናዊ የመገናኛ አማራጮችም በመኖራቸው፣ ሸዋሊድ ዋነኛ የመተጫጫ ቀንነቱን ያጣ ቢመስልም፣ ሁሉም ወደ አደባባይ ወጥቶ የሚገናኝበት ቀን መሆኑ ስላልቀረ፣ በዚች ዕለት ተያይተው ለትዳር የበቁ በርካቶች እንደኾኑ ተሳታፊዎቹ ይናገራሉ።
የሐረሪ ክልል፣ ጀጎልን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ያስመዘገበች፣ የሰላም ከተማ ተብላ የተሰየመች፣ እንዲሁም “የጅብ ምገባ”ን የመሰሉ ትዕይንቶች የምታስተናግድ ከተማ እንደኾነች የሚናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ፣ ሸዋሊድ፥ የሐረሪ ብሔረሰብ በዓል ብቻ መኾኑ ቀርቶ፣ ከሌሎች ጋራ ወንድማማችነትን የምናጠብቅበት በዓል ይኾናል፤ ብለዋል።
በበዓሉ ላይ ከሶማሌ፣ ከኦሮሚያ እና ከአፋር ክልሎች፣ እንዲሁም ከዐማራ ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ፣ ከደቡብ ክልል የስልጤ ዞንና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የባህል ቡድን ተወካዮች ተገኝተዋል።
አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ፣ ሌሊቱን ሙሉ ሳይተኛ በዓሉን በሚያከብርበት የሸዋሊድ ላይ ያገኘናቸው ቱርካዊ ጎብኚ፣ ሐረር በብዙ ነገር ከአገራቸው ጋራ እንደምትመሳሰል ገልጸዋል።
በዚኹ የ“ሸዋሊድ” በዓል ላይ ለመታደም፣ ድሬዳዋ እና ዐዲስ አበባን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ክፍላተ ዓለማት በሺሕ የሚቆጠሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ሐረር ከተማ ገብተዋል።