በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሃማስ ሁለት አሜሪካዊያንን ለቀቀ (የታደሰ)


ጁዲት ራናን እና ልጇ ናታሊ
ጁዲት ራናን እና ልጇ ናታሊ

ዩናይትድ ስቴትስ ሃማስ ካገታቸው ሲቪሎች ሁለት ዜጎቿን ማስለቀቋን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዛሬ አስታውቀዋል።

ሁለቱ አሜሪካዊያን ጁዲት እና ናታሊ ራአናን የሚባሉ እናትና ልጅ መሆናቸውን የእሥራዔል ባለሥልጣናት ቀደም ሲል መግለፃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ለዜጎቻቸው መለቀቅ ካታርና እሥራዔል ስላደረጉት ጥረት ባይደን ምሥጋና አቅርበዋል።

የአሜሪካዊያኑን መለቀቅ አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንም ዛሬ፤ ዓርብ ከቀትር በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ሃማስ አሜሪካዊያኑን የለቀቀው “በሰብዓዊነት ምክንያቶች” እና እሥራዔል ጋዛ ውስጥ እያካሄደች ላለችው ጦርነት “ጠንካራ ድጋፍ እየሰጡ ላሉት ፕሬዚዳን ጆ ባይደን መልዕክት ለማስተላለፍ” እንደሆነ ማስታወቁን ዘገባው ጠቁሟል።

ከሃማስ እገታ የተለቀቁት አሜሪካዊያን በዓለምአቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እጅ መሆናቸውን ቅርበት ያለው ምንጭ እንደነገረው ሮይተርስ ገልጿል።

ከሃማስ ቃል አቀባይ አቡ ኡባይዳ እንደወጣ የተዘገበ መግለጫ “ታጋቾቹ የተለቀቁት ለካታር የማደራደር ጥረት ምላሽ ለመስጠት፣ ስለ ሰብዕና ሲሉና ለአሜሪካና ለዓለም ህዝብም ባይደንና ‘ፋሽስት’ - ሲል የጠራው - አስተዳደራቸው የሚናገሩት ሃስትና መሠረተ ቢስ መሆኑን ለማሳየት ነው” እንደሚል የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

ከታጋቾቹ ብዙዎቹ በህይወት ያሉ መሆኑን የእሥራዔል ጦር ዛሬ ረፋድ ላይ ያስታወቀ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አማካሪ ማርክ ራጌቭም ይህንኑ ለሲኤንኤን አረጋግጠዋል።

ጋዛ ሰርጥ ውስጥ 2.3 ሚሊየን ሰው ያለ ምግብ፣ ያለመድኃኒትና ያለነዳጅ በሙሉ ከበባና መነጠል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሰርጡን እያስተዳደረ ያለውን ሃማስን ሙሉ በሙሉ እደመስሳለሁ የምትለው እሥራዔል እጅግ የበረታ ድብደባ እያካሄደች እንደምትገኝ ተዘግቧል።

ጋዛ ውስጥ እስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 4 ሺህ 137 ፍልስጥዔማዊያን መገደላቸውንና 13 ሺህ ሰው መቁሰሉን የፍልጥዔምን የጤና ሚኒስቴር የጠቀሰው ሮይተርስ አክሎ ዘግቧል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ያለመጠለያ መቅረታቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG