በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ላይ የሚፈፀመው አፈና እንዲቆም ተጠየቀ


 ፋይል፦ አዲስ አበባ /ኢትዮጵያ/
ፋይል፦ አዲስ አበባ /ኢትዮጵያ/

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሀገር ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት እና የሲቪክ ማህበራት ላይ የሚፈፅሙትንና እየተባባሰ የሄደውን አፈና በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አምስት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጥሪ አቀረቡ።

አፈናው በአካል እና በዲጂታል የሚደረግ ክትትልን፣ የቃል ትንኮሳን፣ ማስፈራራትን እና ዛቻዎችን እንደሚያካትት የገለጹት ተቋማቱ፣ እነዚህ ድርጊቶች የሰብዓዊ መብት ተቋማት በሀገሪቱ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር እና ሲጣሱ ደግሞ ተጠያቂነት የማስፈን አስፈላጊ ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ ያግዳቸዋል ብለዋል።

ጥሪውና በጋራ ያቀረቡት አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ወች፣ ፍሮንት ላይን ዲፌንደርስ፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ፌዴሬሽን እና የማሰቃየት ተግባራትን የሚቃወመው ዓለም አቀፍ ድርጅት ናቸው፡፡

ድርጅቶቹ ከቅርብ ወራት ወዲህ የኢትዮጵያ የደህንነት እና የስለላ ኃይሎች፣ አንጋፋ የሆነውን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉን) ጨምሮ በሀገሪቱ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ የሚያደርሱት ስጋት፣ ማስፈራሪያ፣ እና ወከባ መጨመሩን ገልጸዋል።

የመንግስት የደህንነት ኃይሎች እና የስለላ ሰራተኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሰራተኞችን በስራ ቦታቸው እና በመኖሪያ ቤታቸው በመከታተል በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ዘገባቸውን እንዲያቆሙ እንደሚያስገድዷቸውም ድርጅቶቹ አመልክተዋል።

የሲቪል ማህበራትን ዝም ለማሰኘት የሚደረገው ሙከራ በመገናኛ ብዙሃን እና በሌሎች ተቃዋሚ ድምፆች ላይ በሚድርሱ ጥቃቶችም የታገዘ ነው ያሉት ዓለም አቀፍ ተቋማቱ፣ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የመሰብሰብ መብትን ጨምሮ ለሲቪክ እንቅስቃሴዎች የሚሰጠው ቦታ እና ክብር መሸርሸሩን ጠቁመዋል።

ተቋማቱ አክለው የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በአፍሪካ ደረጃ ለተፈረሙ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሕግጋት ተገዢ እንዲሆኑና የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የመንግስት ተቺዎች እና ሌሎች የመብት አቀንቃኞች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG