በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ምዕራብ ወለጋ ውስጥ የተፈፀመው "የዘር ማንነትን የለየ" የተባለ ጥቃት ተወገዘ


ምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ውስጥ ትናንት የተፈፀመውን “የዘር ማንነትን የለየ” የተባለ ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አውግዘው የፀጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈፀመበት አካባቢ መሠማራታቸውንና እርምጃም እየወሰዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

“መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈፀመ ባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልፃለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አክለውም “የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ ‘ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም’ ብለው ተነስተዋል፤ ለዚህም የጥፋት አቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የእነዚያ ኃይሎች ማንነት በስም አልጠቀሱም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው “ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የሚያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።” ብለዋል።

መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች “ሊፈጠሩ ይችላሉ” ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው “ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም” ብለዋል።

“ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን እርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ባወጡት መግለጫ ማጠቃለያ።

በሌላ በኩል ተመሣሣይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “በንፁኃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ኀዘን እገልፃለሁ” ብለዋል በፌስቡክ ገፃቸው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “በተለይ የአማራን ማኅበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው” ብለዋል።

ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ እንደሆነ የጠቆሙት ምክትል ጠቅላም ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግሥትና ህዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

XS
SM
MD
LG