ህገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት በጠቅላላው የአንድን አገር ድንበር አቋርጦ ህገ-ወጥ በሆኑ መንገዶች የተገኙ ገንዘቦች የሚዘዋወሩበት መንገድ ነው። በሙስና፣ በኮንትሮባንድ፣ በወንጀል ድርጊትና ቀረጥ ላለመክፈል የሚዛወር ሂሳብ ነው።
ስሌቱና ቁጥጥሩ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ ለባለሙያዎቹም ቢሆን እራስ ምታት የሆነ ችግር ነው። ቁጥሩ ግን ለማንኛውም ሰው የሚገባና እራስን የሚያስይዝ ነው።
ወደ አፍሪካ አህጉር እስከዛሬ ድረስ በእርዳታ መልኩ ከተለገሰው ገንዘብ ጋር ሲነጻጸር ከአፍሪካ የሚወጣው ህገ-ወጥ ገንዘብ በእጥፍ ይበልጣል።
የግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ (Global Financial Integrity) የተባለ ድርጅትን የሚመሩት ሬመንድ ቤከር አንድ ሰው በህይወቱ ሊያየው ከሚገባ በላይ ከአፍሪካ ገንዘብ በህገ-ወጥ መልኩ ሲወጣ ተመልክቻለሁ፤ በጥናትም አስደግፌ አረጋግጫለሁ ሲሉ በካፒተል ሂል ለተሰበሰቡ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
“በዚህ እክል እንደ አፍሪካ ክፉኛ የተጎዳ የአለም ክፍል የለም። በአለም ዙሪያ ከታዳጊ አገሮች የሚወጣው ህገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት በአመት 1 ትሪሊየን ዶላር ይሆናል፣” ብለዋል።
በተለምዶ የአፍሪካ ሀብት ከሀገር ይዛወራል የሚባለው፤ ለረጅም ጊዜ አገር በሚመሩ አምባ-ገነኖችና አጋሮቻቸው እንደሆነ ይነገራል። ይሄ መንገድ በእርግጥ ብዙ የአገር ሀብት የሚወጣበት ቢሆንም ሌሎች የህገ-ወጥ የገንዘብ ማዛወሪያ መንገዶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ ሬመንድ ቤከር አብራርተዋል።
ከ1970 እስከ 2008 ድረስ ለነበሩት 39 አመታት ከአፍሪካ በህገ-ወጥ መልኩ የወጣው ገንዘብ ወደ 850 ቢሊየን ዶላር ይገመታል። በእርግጥ ይሄ ተመን የማያካትታቸው አጠራጣሪ አሀዞች በመኖራቸው፤ ገንዘቡ ከተባለው ሊበልጥ እንደሚችል ተነግሯል።
በዚህ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ ከ16 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ የሸሸ ሲሆን ከአፍሪካ በ13ኛ ደረጃ ትገኛለች። ለንጽጽር ያህል ጎረቤት ኬንያ 7 ቢሊየን ዶላር (22ኛ) ጅቡቲ 1 ቢሊየን ዶላር (45ኛ) ኤርትራ 117 ሚሊዮን ዶላር (51ኛ) ደረጃን ይዘዋል።
በአፍሪካ ከፍተኛ ገንጸብ በህገ-ወጥ መልኩ የሚወጣባት አገር ናይጀሪያ ስትሆን 241 ቢሊየን ዶላር፣ ግብጽ 131 ቢሊዮን፣ ደቡብ አፍሪካ 74 ቢሊየን ዶላር በመሆን ከ1-3 የለውን ስምን በበጎ የማያስጠራ ሰንጠረዥ ተቆናጠዋል።
ሬመንድ ቤከር የሚሰሩበት ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ ድርጅት ከአፍሪካ አገሮች ጋር ይህንን ወንጀል ለማስቆም አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኢሲኤ እንዲሁም የገንዘብና የልማት ሚኒስትሮች ጋር በአንድነት አፍሪካ የህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ልትቆጣጠር የምትችልበትን መንገድ ለማብጀት ይንቀሳቀሳል።
የጥምረት ስራው ገና በንግግር ደረጃ ላይ ይገኛል። አፍሪካ የገንዘብ ዝውውርን የሚከታተል ኮሚሽን እንድታቋቁምና የአፍሪካ መሪዎች አንድ የመወያያ አጀንዳ አድርገው መፍትሄ ለማበጀት ንግግር እንዲጀምሩ ጥረት ተጀምሯል።