በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ለየት ያለ የዜማ ቃናን ካስተዋወቁ የ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ኮከብ ዜመኞች መካከል አንዱ የነበረው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
በ1936 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መርካቶ የተወለደው ጌታቸው፣ ግማሽ ምእት ዓመትን በተሻገረው ሞያዊ ሕይወቱ፣ ልዩ ትርጉም ያላቸውን ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎችን ለአድማጮች አበርክቷል።
በጣልያንኛ እና እንግሊዘኛ ዜማዎች የአዳጊነት ዘመን ልብ እና አእምሮው ለሙዚቃ እንደተነሣሣ ጌታቸው ካሳ ተናግሯል፡፡ ኾኖም የሙዚቃ ዝንባሌውን ቤተሰቦቹ አልደገፉለትም፡፡ እንዲያውም አባቱ በስማቸው(በጸጋዬ) እንዲጠራ ባለመፈለጋቸው ጌታቸው የአባቱን ስም ለመለወጥ እስከ መገደድ ደርሷል።
የሙዚቃ ፍቅሩ ከቤተሰቡ ያቃቃረው ጌታቸው ታዲያ፣ ባቀናባቸው ድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞች፣ “ሰጎን ኦኬስትራን” ከመሰሉ የዜማ ቡድኖች ጋራ በመሥራት የድምፃዊነት ክህሎቱን አጎልብቷል።
ጌታቸው ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ፣ የሙዚቃ አድማሱን በተደራጀ ኹኔታ ያሰፋው፣ በ1960ዎቹ ከ“ፈጣን ባንድ” ጋራ ባደረገው ጥምረት ነው። በይቀጥላልም፣ በዘመኑ ዕውቅ ከነበሩት ሸበሌ ባንድ እና ዋሊያስ ባንድ ጋራ ለመሥራት ችሏል። የውቤ በረሓ ድምቀት በነበረው “ፓትሪስ ሉሙምባ” የምሽት ክበብ እና ሰንጋ ተራ ላይ ነግሦ በኖረው ሶምበሪኖ ክለብ፣ ተናፋቂ የዘመኑ ድምፃውያን መካከል አንዱ ጌታቸው ካሳ ነበር።
በ1970ዎቹ አምኃ እሸቴን ከመሰሉ የሙዚቃ አሳታሚዎች ጋራ ወዳጅነት የፈጠረው ጌታቸው፣ በአምኃ፣ ካሊፋ እና ፊሊፕስ ድርጅቶች አማካይነት አምስት ነጠላ ዜማዎችንና ሸክላዎችን ለአድማጮች አድርሷል።
በ1973 ዓ.ም. ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለሥራ ያቀናው ዕውቁ ድምፃዊ፣ በስደት ሕይወት ውስጥ ለ27 ዓመታት ቆይቷል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ትውልደ አሜሪካውያን መድረኮች እና የመዝናኛ ስፍራዎች ውስጥ፣ በተናጠል እና ከሌሎች ድምፃውያን ጋራ ሥራዎቹን አቅርቧል።
በኢትዮጵያ ዕሥራ ምእት(ሚሊኒየም) ማግስት ወደሚወዳት ሀገሩ ኢትዮጵያ ማንነቱን እንደጠበቀ የተመለሰው ጌታቸው፣ በቀጣይ ዓመታት በተለያዩ መድረኮች ላይ ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ሥራዎቹን አቀንቅኗል።
ጌታቸው፡- “የከረመ ፍቅር” እና “ብርቱካን ነሽ ሎሚ” በሚሉ ዜማዎቹ የአፍቃሪያንን ሕመም አስታሟል። “ሀገሬ ትዝታሽ” እና “አዲስ አበባ” በሚሉ ዜማዎቹ ደግሞ የሀገር ፍቅር ናፍቆትን ከጀግና ኢትዮጵያውን መታሰቢያ ጋራ አሰናኝቶ አቅርቧል። “እመኛለሁ!” የሚለውን የመሰሉ ዜማዎች ደግሞ “ኑሮን ከብልሃቱ” ማስማማት ላቃታቸው የመንፈስ አጋርነቱን አሳይቷል።
ጌታቸው በልዩ ቃናው እና ላኅዩ ብቻ ሳይኾን፣ በመድረክ ውዝዋዜው እና የአዘፋፈን ስልቱ የራሱን አሻራ በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ መፍጠር የቻለ ቄንጠኛ ድምፃዊ እንደኾነም ይነገርለታል። የሠራቸውን ዜማዎች ቁጥር ራሱም ለመናገር እስኪያዳግተው ድረስ በርካታ እንደኾኑም
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሕመም ውስጥ ስለመቆየቱ የተነገረለት አንጋፋው ድምፃዊ፣ በየካቲት 12 ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ ትላንት የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊት በ79 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ታውቋል።
አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ፣ የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው፡፡
መድረክ / ፎረም