በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ እህል ከዩክሬን እንዳይጫን ማገዷን እንድታጤነው ጀርመን በድጋሚ ጠየቀች


ፎቶ ፋይል፦ የስንዴ ሰብል ሲሰበሰብ ዙጉሪቭካ፣ ዩክሬን፤ እአአ ሐምሌ 9/2022
ፎቶ ፋይል፦ የስንዴ ሰብል ሲሰበሰብ ዙጉሪቭካ፣ ዩክሬን፤ እአአ ሐምሌ 9/2022

ሩሲያ፣ እህል ከዩክሬን የሚወጣበትን ስምምነት እንዳቋረጠች ማስታወቋን ተከትሎ፣ ጀርመን ጉዳዩን እንድታጤነው ሩሲያን ዳግመኛ ጠይቃለች፡፡

የጦር ወቅት ስምምነቱ፥ የረኀብ ስጋት ወዳጠላባቸውና የምግብ ዋጋ ውድነት ተጨማሪ ሰዎችን ወደ ድህነት ወደገፋባቸው፣ የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የእስያ ሀገራት፣ እህል ከዩክሬን እንዲገባላቸው አስችሎ ነበር።

የራሷን እህል እና ማዳበሪያ፣ ለዓለም ገበያ ለመላክ ያቀረበችው ጥያቄ እስኪሟላ ድረስ፣ ሩሲያ ስምምነቱን እንዳቋረጠች፣ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል።

የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ክሪስቲያን ሆፍማን፣ ሩሲያ ስምምነቱን እንድታስረዝምና በዓለም ድኻ የኾኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጎዳ ርምጃ እንዳትወስድ እንጠይቃለን፤ ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዩክሬን፥ ከአሜሪካ ያገኘችውን ክላስተር ቦምብ በሩሲያ ኃይሎች ላይ ከተጠቀመች፣ ሩሲያም ያላትን በቂ ክምችት ለጦርነቱ እንደምታወጣ፣ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ትላንት አስታውቀዋል።

ዩክሬን፣ ክላስተር ቦምቦቹን፣ ወደ ግዛቷ በገቡ የሩሲያ ወታደሮች ላይ ብቻ እንደምትጠቀም አስታውቃ ነበር፡፡

ቦምቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል፣ ከ100 ሀገራት በላይ በፈረሙት ዓለም አቀፍ ስምምነት ታግዷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG