በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከምዕራብ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ ጌዲዖዎች በረሃብ እየተሰቃዩ መሆኑን ገለፁ


ካለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በጊዲዖ ዞን በገደብ ወረዳ፣ በጎቲቲ ቀበሌ፣ ባንቆራ፣ ጮርሶ፣ ቀርጫ፣ ይርጋጨፌና ዲላ ውስጥ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች፤ ለስምንት ወራት ያህል የምግብ ርዳታን ባለማግኘታቸው ለረሃብና ለተላላፊ በሽታ መጋለጣቸውን ገለፁ። በረሃቡ የሞቱ ሕፃናት አሉ ብለዋል።

የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ በገደብ ወረዳ ጎቲቲ ቀበሌ ስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ ተፈናቃዮቹን እንዳነጋገረው፤ ተፈናቃዮቹ ለወራት ለምግብ እጥረት በመጋለጣቸው ሕፃናት ሕይወታቸው ማለፉን፣ በረሃብና በተላላፊ በሽታ መጠቃታቸውን ተናግረዋል። እናቶች፣ አራሶች፣ ሴቶችና ሕፃናት የሚበሉት በማጣታቸው ለስቃይ መዳረጋቸውን ገልፀዋል። በተለይ በጎቲቲ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ተፈናቃዮች ከገጠማቸው የከፋ የምግብ ችግር የተነሳ ሰውነታቸው ከስቶና ገርጥቶ ይታያሉ። በቆዳቸው ላይም የእከክ በሽታ አጋጥሟቸዋል።

የጊዲዖ ዞን በአሁኑ ሰዓት መዝግቦ በያዘው መረጃ መሰረት ከምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት ተፈናቃዮች 178 በላይ ሺሕ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው 40 ሺሕ መሆናቸውን የጌዲዖ ዞን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትዕግስቱ ገዛኸኝ ተናግረዋል። በረሃቡም ምክኒያት ሦስት ሕፃናት ሕይወታቸው ማለፉን አረጋግጠዋል። እስካሁ ለምን የምግብ እርዳታ እንዳልተደረገ ተጠይቀው፤ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ተደርገው እንደነበርና የእርዳታ እህሉም በያሉበት ሲላክ እንደነበር ገልፀው በየጊዜው አዲስ ተፈናቃዮች ስለሚገቡ የመረጃ ችግር እንደነበረቻቸው ተናግረዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ትናንት ሲናገሩ፤ ከደቡብ ክልል የእርዳታ ጥያቄ የቀረበላቸው በመጋቢት ወር እንደሆነ ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት አቶ ነጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው፤ መንግሥት ለተፈናቃዮቹ የዕለት ምግብ ለማድረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ጉዳዩን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚከታተሉ የተለያዩ ሰዎችም ለተጎጂዎቹ የምግብ እርዳታ እንዲደርስ ለማድረግ ገንዘብ የማሰባሰቢያ መድረኮችን ከፍተው ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። (ዘጋቢያችን ዮናታን ዘብዲዮስ በመጠለያ ካምፖቹ ተገኝቶ ያጠናቀረው ዘገባ እንደደረሰን እናቀርባለን)

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG