በጋዛ ጦርነት የተፈናቀሉ በርካታ ፍልስጤማውያን የተኩስ አቁም በመጠየቅ ዛሬ ረቡዕ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
በማዕከላዊ ጋዛ፣ ዲር አል ባላህ በተባለው ሥፍራ በተካሄደው ተቃውሞ የተገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች እና ህጻናት፣ በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል ወደ ሚገኘው ቤታቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
በከሻቲ የስደተኞች ካምፕ የሚገኘው ተፈናቃዩ እስማኤል ሃሶና፣ "ወደ ቤታችን ተመልሰን መደበኛ ህይወታችንን መቀጠል እንፈልጋለን። እንደማንኛውም የዓለም ህዝብ በሰላም የመኖር መብት አለን” ሲል ለአሶሴይትድ ፕሬስ ተናግሯል፡፡
ሌሎች ተፋናቃዮችም ለአሶሴይትድ ፕሬስ ጨምረው እንደተናገሩት በከፍተኛ የምግብ ውድነትና እጥረት እንደተቸገሩና ደህንነቱ ያልተጠበቀ መጠለያ ውስጥ በመሆናቸው ኑሯቸው ስቃይ የተሞላበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወደ ቤታችን ተመልሰን መደበኛ ህይወታችንን መቀጠል እንፈልጋለን። እንደማንኛውም የዓለም ህዝብ በሰላም የመኖር መብት አለን”
ተቃውሞው የተካሄደው የእስራኤል ኃይሎች በጋዛ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሚገኘው ዋና ሆስፒታል አጠገብ ከፍልስጤም ታጣቂዎች ጋር እየተዋጉ ባሉበት ወቅት ሲሆን፣ የህክምና ባለሙያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ሰዎች ከግጭቱ መውጫ አጥተው እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡
እስራኤል 3 ወር የፈጀውን ጥቃት በሐማስ ላይ በመክፈት ወደፊት እየገፋች ባለችበት ወቅት፣ ነዋሪዎች ናስር ሆስፒታልን እና ሁለት ትናንሽ የህክምና ተቋማትን ያካተተውን የካን ዮኒስን የመሀል ከተማ ክፍል እንዲለቁ አዛለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ)፣ አካባቢው የ88,000 ፍልስጤማውያን መኖሪያ መሆኑን እና በሌላ ቦታ በተካሄደ ጦርነት የተፈናቀሉ ሌሎች 425,000 ሰዎችን እያስተናገደ እንደሆነ ገልጿል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ቢያንስ 210 ፍልስጤማውያን መሞታቸውንና አጠቃላይ በጦርነቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 25,700 መድረሱን በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል። ቁጥሩ በሲቪሎች እና ተዋጊዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለይቶ ያመለከት ባይሆንም፣ አብዛኞቹ የሞቱት ሴቶች እና ህጻናት ናቸው ብሏል ሚኒስቴሩ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለስልጣናት፣ ቢያንስ አንድ አራተኛ የሚሆነው ህዝብ ለረሃብ እየተጋለጠ እንደሆነ እና ብዙ ሰዎችም በበሽታ ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
መድረክ / ፎረም