በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋምቤላ የሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ


በጋምቤላ የሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:51 0:00

ከደቡብ ሱዳን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሙርሌ ታጣቂዎች፣ ጋምቤላ ውስጥ ዐሥር ሰዎችን ገድለው 12ቱን ማቁሰላቸውን፣ የክልሉ የጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።

ታጣቂዎቹ፥ በኑዌር ዞን፣ ዋንቱዋ ወረዳ፣ መተሐር ከተማ በምትገኘው መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንና በማኩዌይ ወረዳ፣ ቢልኬች ቀበሌ ገብተው ጥቃት እንደፈጸሙ፣ የክልሉ የጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።

ባለፈው ቅዳሜ፣ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ማምሻውን፣ ከደቡብ ሱዳን ድንበር አቋርጠው የገቡ የሙርሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት፣ 10 ሰዎች መገደላቸውን ያረጋገጡት፣ የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ኡቶዉ ኡኮት፣ የቆሰሉት 12 ሰዎች፣ በጋምቤላ ሆስፒታል ሕክምና በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

መተሐር ከተማ እና ቢልኬች ቀበሌ፣ ታጣቂዎቹ፣ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚሻገሩበት ድንበር መኾኑን የገለጹት ሓላፊው፣ በሌላ አካባቢ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ ለአሠሣ እንደተሰማሩ አመልክተዋል፡፡

የሙርሌ ጎሣ ታጣቂዎች፣ በኢትዮጵያ ላይ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት መፈጸማቸው ሲነገር፣ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው በመግባት፣ ሰላማዊ ሰዎችን እንደሚገድሉና ሕፃናት ልጆችንም ጠልፈው እንደሚወስዱ፣ የአሜሪካ ድምፅን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መዘገቡ ይታወሳል።

ይህንኑ የልጆች ጠለፋ ድርጊት፣ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዚያው በደቡብ ሱዳን ውስጥም እንደሚፈጽሙ፣ የአካባቢው ቃል አቀባይ ጃይ አዲንጎራናይ፣ ከዚኽ ቀደም ለአሜሪካ ድምፅ አመልክተዋል።

የሙርሌ ጎሣ ታጣቂዎች፣ ወቅት እየጠበቁ ለሚፈጽሙት የጠለፋ ድርጊት፣ በምን ዐይነት የመፍትሔ አማራጭ እልባት መስጠት እንደሚቻል የተጠየቁት ሓላፊው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

በታጣቂዎቹ የጠለፋ ድርጊት እና ድርጊቱን ለመከላከል እና የተጠለፉትን ለማስመለስ በሚካሔደው ግጭት የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከሚሊሻ አባላት ጋራ በመኾን፣ ክትትል እያደረጉ

እንደሚገኙ አቶ ኡቶዉ አመልክተዋል፡፡ ክልሉም፣ የጸጥታ ኃይሉን በማቀናጀት፣ በጥቃት አድራሾች ላይ ወሳኝ ርምጃ በመውሰድ፣ ሰላምንና ጸጥታን የማስከበር ሥራ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የክልሉን ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክን ጨምሮ ልዩ ልዩ ባለሥልጣናት፣ በኑዌር ዞን በዋንቱዋ እና በማኩዌይ ወረዳዎች ተገኝተው፣ ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳበረታቱ፣ አቶ ኡቶዉ አክለው ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG