በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋምቤላ ውስጥ በተጣለ አደጋ አምስት ሰው ተገደለ


ጋምቤላ
ጋምቤላ

ከጋምቤላዋ ፉኝዶ ከተማ ወደ ደቡብ ሱዳኗ ፖቻላ አውራጃ (ካውንቲ) ይጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ ተከፍቶ ቢያንስ አምስት ሰው መገደሉና ሌሎች ስምንት መቁሰላቸው ተሰማ፡፡


ከጋምቤላዋ ፉኝዶ ከተማ ወደ ደቡብ ሱዳኗ ፖቻላ አውራጃ (ካውንቲ) ይጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ ተከፍቶ ቢያንስ አምስት ሰው መገደሉና ሌሎች ስምንት መቁሰላቸው ተሰማ፡፡

ጥቃቱ የተጣለው ዛሬ - ረቡዕ፣ ግንቦት 7 እኩለ ቀን ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ተኩሱን የከፈቱት የሞርሌ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ታጣቂዎች መሆናቸውን የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎርደን ኮንግ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

ከተገደሉት መካከል አንድ የግብርና ባለሙያና አንዲት ሴት እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

በተሽከርካሪው ውስጥ ከተሣፈሩት መካከል ሰባቱ የደቡብ ሱዳን ሰዎች እንደነበሩና የተገደሉትም በሙሉ ደቡብ ሱዳናዊያን መሆናቸውን የፀጥታ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚኖሩት የሞርሌ ጎሣ አባላት በተደጋጋሚ ጊዜ በተለይ በበጋ ወራት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እየዘለቁ የሰው ጠለፋ፣ ግድያና ዘረፋም እንደሚያካሂዱ አቶ ጎርደን ኮንግ ገልፀው ካለፈው የካቲት እስከ ሚያዝያ መጨረሻ በነበረው ጊዜ ውስጥ ብቻ ከሃያ በላይ ሰው መግደላቸውን፣ 14 ሕፃናትን ጠልፈው መውሰዳቸውን፣ ወደ 18 ሰው ማቁሰላቸውንና ከ950 በላይ ከብት መዝረፋቸውን ዘርዝረዋል፡፡
ጥቃቱን ለማስቆም የክልሉ መንግሥት በሚሊሽያና በፖሊስ ኃይል ጥረት እያደረገ መሆኑንም የፀጥታ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ዝርዝሩን ግርማይ ገብሩ ከመቀሌ በስልክ ያጠናቀረው ዘገባ ይዟል፤
ከድምፅ ፋይሉ ያዳምጡ፡፡
XS
SM
MD
LG