በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የ"መርከል ዕቅድ" ለአፍሪካ ልማት ሊቀርብ ነው


የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል
የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል

በብልጥግና የናጠጡት ሃገሮች አፍሪካ ላይ የሚፈስሰውን እርዳታና መዋዕለ-ነዋይ በሚመለከት አዲስ ዓይነት አካሄድ እንዲከተሉ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል አሳስበዋል፡፡

በብልጥግና የናጠጡት ሃገሮች አፍሪካ ላይ የሚፈስሰውን እርዳታና መዋዕለ-ነዋይ በሚመለከት አዲስ ዓይነት አካሄድ እንዲከተሉ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል አሳስበዋል፡፡

"የመርከል ዕቅድ" ተብሎ የተሰየመው ሃሣብ አፍሪካ ውስጥ ብዙ መዋዕለ-ነዋይ የማፍሰስ ጥሪ ወደ አውሮፓ የሚጎርፈውን የአፍሪካዊያን ስደት ያስቆማል የሚል ዕምነት ሰንቋል፡፡

የአፍሪካ ምጣኔ ኃብቶች እንዲመነደጉ ማገዝ ለአፍሪካ ሲባል የሚቸር እርዳታ አይደለም - የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር ያስተላለፉት መልዕክት ነው - ይልቅ የድኅነት ማዕበል የሚያሳድደውንና ወደ አውሮፓ የሚገፋውን አፍሪካዊ ባለበት እንዲያልፍለት የሚያደርግ እጅግ አስፈላጊና ቁልፍ እርምጃ እንጂ!!

አንዳች መፍትኄ ካልተበጀና የተግባር ጣልቃ ገብነት ካልተደረገ መቶ ሚሊየን አፍሪካዊ ፍልሰተኛና ስደተኛ ጀርመንን ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያጥለቀልቃት እንደሚችል ምዩለር ሥጋታቸውን አሰምተዋል።

ቻንስለር አንጌላ መርከል በአፍሪካ ኢንቨስትመንቶች ላይ 335 ሚሊየን ዶላር ለማፍሰስ አቅደዋል፤ /በዛሬ ምንዛሪ ከ7 ቢሊየን 720 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር በላይ መሆኑ ነው፡፡/ የተቀሩት አሥራ ዘጠኝ ቱጃር ሃገሮችም በመጭው ሣምንት ጀርመን ውስጥ ሲሰበሰቡ ቀና ማለት አቅቷቸው መሬት ለመሬት የሚድበሰበሱና ለማንሠራራት ሲፍጨረጨሩ የሚታዩ የአፍሪካ ምጣኔኃብቶችን እንዲያግዙ የበርሊንን አርአያ እንዲከተሉ ጥሪ እንደሚያደርጉ መርከል ተናግረዋል፡፡

ለጊዜው ጀርመን በቅድሚያ የኢንቨስትመንት ትኩረት ዝርዝሯ ውስጥ የሠፈረቻቸው አራት የአፍሪካ ሃገሮች አይቮሪ ኮስት፣ ሞሮኮ፣ ርዋንዳና ቱኒዝያ ቢሆኑም ዶ/ር መርከል በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሌሎችም የአህጉሪቱ መሪዎች ጋር መወያየታቸው ታውቋል፡፡

ጀርመን አፍሪካ ውስጥ የነበራትን ሁከትና ኃይል የበዛበት የቅኝ ገዥነት ገፅታዋን ለመቀየርና ይልቅ እንደ ንግድና ሥራ አጋርና መሪ ለመውጣት በብርቱ እየሠራች ነች ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የዓለምአቀፍ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ምጣኔኃብታዊ ዲፕሎማሲ መርኃግብር ዳይሬክተር ታሊታ በርትልስማን-ስኮት ካብ ካብ አድርገዋታል፡፡

"ጀርመን ብዙ ሰጥታለች፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የፋብሪካ ምርቶች መሪ ኃይል ሆና ብዙዎችን አነቃቅታለች። አፍሪካዊያንም በኢንዱስትሪ የሚራመዱባቸውን መንገዶች እየፈተሹ ነው፡፡ በዚህ በኩል ጀርመን መሪ እየሆነች ነው" - በበርተልስማን አባባል፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን በጀርመን የገንዘብ ሚኒስቴር በተነደፈው ዕቅድ ላይ ጥቂት ቅሬታ ወይም ሥጋት እንዳላቸው በርተልስማን-ስኮት አመልክተዋል፡፡ ከአፍሪካ ሃገሮች ጋር አንዳችም ምክክር አልተደረገበትም ነው የመቆጠባቸው ምንጭ፡፡

ከሠሃራ በስተደቡብ ባሉ ሃገሮች ውስጥ ንግዶችን መጀመርና ማያያዝ ላይ የምክር አገልግሎት የሚሰጠው ዋና መሥሪያ ቤቱ ጀርመን የሚገኘው አፍሪኮን የሚባል ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ማርክ ዛንደር ከሽቱትጋርት - ጀርመን ለቪኦኤ እንደተናገሩት አፍሪካ ውስጥ ጠበቅ ያሉና የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንቶችን ለመመሥረት የሚፈልጉ ጀርመናዊያን ኩባንያዎች በየዕለቱ እየበረከቱ ነው፡፡

"ብዙዎቹ የጀርመን ኩባንያዎች በቤተሰብ የተያዙ በመሆናቸው አፍሪካን የሚመለከቷን በአንድ በኩል በጥንቃቄ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሊከተሏቸው በሚችሉ ስልቶቻቸውና በተራዘመ ጊዜ እያሰቡ ያሉ ኩባንያዎችም ብዙ ናቸው" ብለዋል ዛንደር፡፡

በነገራችን ላይ ዛሬ አፍሪካ ውስጥ በተለያዩ ሃገሮች ውስጥ እየሠሩ ያሉ ወደ ስድስት መቶ የሚሆኑ ጀርመናዊያን ኩባንያዎች አሉ፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ ያድጋል የሚል ዕምነት እንዳላቸው በርሊን የሚገኘው ጀርመን-አፍሪካ የንግድ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክሪስቶፍ ካኔንጊሰር ተናግረዋል፡፡ የጀርናዊያኑን ንግዶች ወደ አፍሪካ ከሚስቡ አበረታች ገፅታዎች መካከል በፍጥነት እያደገ ያለው ሕዝቧና በዚህም ምክንያት የሚፈጠረው የተጠቃሚና የገበያ መስፋት መሆኑን ካኔንጊሰር አክለው ጠቁመዋል፡፡

"ከሁሉም በፊት አፍሪካን በሚመለከት ጀርመን ያላት አዲስ አካሄድ አፍሪካ እጅግ በበለጠ ሁኔታ የፖለቲካና የምጣኔኃብት ኃይል መሆኗን ነው፡፡ እናም ጀርመን ከአፍሪካ ጋር በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ቁልፍ ከሆኑ የአፍሪካ ሃገሮች ጋር ትስስሮችን ማጥበቅ፣ እንዲሁም እጅግ የተጠከሩና የሰፉ ግንኙነቶቿን መገንባት ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ አፍሪካን የምጣኔኃብት ዕድሎች ያሉባት አህጉር መሆኗን መገንዘብና በተግባርና በአካልም መሣተፍ ነው" ብለዋል፡፡

የባለ ብዙ ወረትና ኃይል ሃያ ሃገሮች «ቡድን ሃያ» ወይም "ጂ ሴቭን" ስብሰባ የፊታችን ሰኔ 30 እና ሐምሌ 1 የጀርመኗ ሃምቡርግ ከተማ ላይ ይካሄዳል፡፡

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

የ"መርከል ዕቅድ" ለአፍሪካ ልማት ሊቀርብ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:25 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG