ብሪታኒያ፣ ፈረንሣያና ጀርመን በኢራን የኒኩሌር መርሃግብርና የተምዘግዛጊ ሚሳይሎች ምርት ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ በቴህራንና በዓለም ኃያላን መንግሥታት መካከል ተፈርሞ በነበረውና በተስተጓጎለው የኒኩሌር ስምምነት መሠረት የፊታችን ጥቅምት ውስጥ ማብቃት እንደነበረበት ተመልክቷል።
ሦስቱ የአውሮፓ አጋሮች የኒኩሌር ስምምነቱ ድርድር እንዲሳካ ሲያግዙ እንደነበር ይታወቃል።
“ኢራን ስምምነቱን ባለማክበር በተከታታይ ለፈፀመችው ጥሰት ቀጥተኛ ምላሽ ለመስጠት” በሚል በማዕቀባቸው እንደሚቀጥሉ ሦስቱ ሀገሮች ያስታወቁት ትናንት ሐሙስ በሰጡት የጋራ መግለጫ ነው።
ኢራን የተጣለባትን እገዳ በመጣስ የተምዘግዛጊ ሚሳይሎች ሙከራ ታደርጋለች፤ ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ለምታካሂደው ጦርነትም ድሮኖችን ለመስኮብ ትልካለች የሚል ክስ ቀርቦባታል።
“የሃገሮቹ ውሳኔ ትብብርን የሚጎዳ፣ ህገወጥ እና ተንኳሽ እምርጃ ነው” ሲል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ የኢራን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ዋሺንግተን ስለቀጣይ እርምጃ ከአውሮፓ አጋሮቿ ጋር እየተነጋገረች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ሃገራቸውን ከኢራኑ የኒውክለር ስምምነት የዛሬ አምስት ዓመት ማስወጣታቸው የሚታወስ ሲሆን የአሁኑ የባይደን አስተዳደር ስምምነቱን ለማስቀጠል ያደረገው ጥረት እስካለፈው ወር ሳይሳካ መቅረቱን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
መድረክ / ፎረም