በሰው ልጅ አመጣጥ አጥኝዎች ዘንድ ከሰው ልጅ የቀደሙት በሚባሉት ከሰው ተፈጥሮ ጋር ዝምድና ባላቸው እና በዛሬው የሰው ልጅ መካከል የሚገኝ ዝርያ ነው የተባለ የመጀመሪያው ሰው ቅሪተ-አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኝቷል፡፡
መገኘቱ ከረቡዕ፤ የካቲት 25/2007 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም መገናኛ ብዙኃን በስፋት እየተነገረ ያለው ይህ “የመጀመሪያው ሰው ቅሪተ-አካል ነው” የተባለ መንጋጭላ የሁለት ሚሊየን ስምንት መቶ ሺህ ዓመት ዕድሜ ያለው እንደሆነ ታውቋል፡፡
የዝንጀሮ ዓይነት ተፈጥሮ የነበራቸው ከሰው የቀደሙት ፍጡራን የአየር ንብረት መለዋወጥ ባስከተለባቸው የተፈጥሮ አካባቢ ጫና ምክንያት ከዛፍ ላይ ወርደው መሬት ላይ መኖርና ቀጥ ብለውም መሄድ ስለመጀመራቸው የነበረውን ሃሣብ ግኝቱ አጠናክሮታል፡፡
እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ ዝርያዎች ይኖሩ የነበረው ሉሲ ወይም ድንቅነሽ ተብላ የተጠራችው ፍጡር ቅሪተ-አካል በነበረበት አካባቢ መሆኑ ታውቋል፡፡
የሉሲ ዕድሜ 3.2 ሚሊየን ዓመት ሲሆን የአሁኑ ቅሪተ-አካል የተገኘው ተመሣሣይ የሰው ዝርያዎች ሊኖሩበት ይችላሉ ብለው ተመራማሪዎቹ ገምተውት ከነበረበት ጊዜ በአራት መቶ ሺህ ዓመት ቀድሞ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአሁኑ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ቅሪተ አካል መገኘት ኢትዮጵያ በእውኑ የሰው ልጅ መገኛ ነች የሚለውን መላ ምት ይበልጥ እያጠናከረው መጥቷል፡፡