ከዚህ ቀደም ከአማራ ክልል ሄደው በደቡብ ክልል ጉራ-ፈርዳ ይኖሩ የነበሩ አርሦአደሮችና ቤተሰቦቻቸው በአካባቢው ባለሥልጣናት «ህገ-ወጦች» በመባላቸው የመሬት ይዞታዎቻቸውን እያስረከቡ መባረራቸው ይታወሳል።
ዘንድሮም ተመሣሣይ የአርሦአደሮች ኢትዮጵያዊያን መሰደድና መፈናቀል እንደቀጠለ መሆኑ እየተሰማ ነው።
ለዓመታት ኑሯቸውን በቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል ያደረጉ ቤት ንብረት የመሠረቱ፣ ልጆች፣ የልጅ ልጆች ያዩበትን ቀዬ እንዲለቅቁ መገደዳቸውን እራሣቸው ተፈናቃዮቹ ተናግረዋል።
የተሰጠን ምክንያት «ህገ-ወጥ ናችሁ» የሚል ነው ይላሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ እኛም ሰሞኑን እየዘገብንበት እንገኛለን።
በህጉ ረገድ ጉዳዩ እንዴት ይዳኛል? ለሚለው ጥያቄ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓለምአቀፍ ህግ አስተማሪና፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም ልዩ ልዩ የህግ ኮርሶች የሚሰጡት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያምን አግኝተናል።
ዶ/ር ያዕቆብ በርዋንዳ የተካሄደውን የጅምላ ዘር ፍጅት ክሥ በዐቃቢህግነት ያያዙ ባለሙያም ናቸው።
ያወያያቸው አዲሱ አበበ «ይህ ጉዳይ ከዓለምአቀፍም ሆነ ከኢትዮጵያ ህግጋት አኳያ እንዴት ይታያል?» በሚለው ጥያቄ ነው የጀመረው፤