በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ጉባኤ ሲተነተን


“የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ቋንቋን ወይንም ብሄር ብሄረሰብን መሰረት አድርጎ በመከፋፈል አይሳካም” ልደቱ አያሌው

“የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ቋንቋን ወይንም ብሄር ብሄረሰብን መሰረት አድርጎ በመከፋፈል አይሳካም” ልደቱ አያሌው

ሰሞኑን ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን፤ በተለይ በመንግስቱ ቁጥጥር ስር የሚገኙት የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጣቢያዎች “ብሄር ብሄረሰቦች…” የሚሉ ሙዚቃዎች ያሰማሉ፣ ቃለ-መጠይቅ ይደረጋል፣ በዋና ከተማዋ የሙዚቃና የባህል ስነስርዓቶች ይሰናዳሉ።

በየዓመቱ ከሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በተያያዥነት 5ኛው የዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በዚህ ዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ጉባኤ በርካታ አስተሳሰቦች ተስተናግደዋል። ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተሰባሰቡት የጉባዔው ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በፌዴራሊዝም ስርዓት ግንባታ ያሳየችውን ለውጥ አወድሰዋል።

በተጓዳኝ በኢትዮጵያ የተገነባው የፌዴራል ስርዓት መሰረታዊ የሆነውን የፌዲራሊዝም ራእይ ያጨናገፈ ነው ብለው የሚያምኑም ጥቂት አይደሉም።

በፌዴራሊዝም ሰፊ ጥናት ያደረጉት ኤፍሬም ማዴቦ ፌዴራሊዝም የፖለቲካ ስልጣን ከማእከል ተፈፍሎ የሚወጣበትና ክልሎችና በጠቅላላው ዜጎች የስልጣኑ ተካፋይ ሚሆኑበት ስርዓት ነው ይላሉ። “እነዚህን ነገሮች በግልጽ ኢትዮጵያ ውስጥ አናያቸውም። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ በፌደራሊዝም ስም አሃዳዊ ስርዓት እንዳለ ነው የምረዳው” ይላሉ ኤፍሬም ማዴቦ።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በቀድሞ ስርዓቶች የነበረው አሃዳዊ አገዛዝ በአንድ አገር ጥላ ያሰባሰበው ብሄራዊ ውክልና የሌላቸው “የአንድ አገር ህዝቦች” በሚል መርህ ብዝሃ-ሰብን ያጠፋ ነው ይላል። አቶ መለስ ዜናዊ በ5ኛው አለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ጉባኤ ላይ የሚከተሉት ፌደራሊዝም “ወደ ብሄራዊ ህዳሴ የሚያመራ ትክክለኛ መንገድ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝደንት አቶ ልደቱ አያሌው በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችን በቋንቋ የመናገር፣ የመማር፣ የመዳኘትና የመሳሰሉት መብቶች ከፌዴራሊዝም ጋር የማጣመር የተሳሳተ አመለካከት አለ ይላሉ።

ዩናይትድ ስቴይትስ የፌዴራል መንግስት ሆና ብሄር ብሄረሰብ የሚባል ነገር የላትም የሚሉት አቶ ልደቱ በኢትዮጵያ የሚዘረጋው የፌደራል ስርዓት ዋናው አላማ “ስልጣንን ወደታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የማድረስ ጉዳይ ነው” ይላሉ።

“በህገመንግስት ደረጃ ተቀምጧል፤ በተግባር ስናይ ግን ከጀርባ በአንድ ሃይል በከፍተኛ ደረጃ ማእከላዊነትን በሚጠብቅ ፓርቲ ቁጥጥር ስር ነው ስልጣን ያለው” ብለዋል አቶ ልደቱ። አክለውም የሀብት ክፍፍልን በተመለከተ የቀረጥና የተፈጥሮ ሃብቶችን በዋነኝነት የሚያስተዳድረው ማእከላዊ መንግስት ነው ይላሉ።

አቶ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ያለው የፌዴራል አስተዳደር ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት “የባለ ሁለት ዲጂት” የኢኮኖሚ እድገት አይነተኛ አስተዋጾ አበርክቷል ሲሉ ተናግረዋል። በእርግጥ የዜጎችን ኑሮ፣ መብት፣ የራስን ማስተዳደር መብት ቢሰጥም፤ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ የተዋጣለት ነው ማለት እንደማይቻል አቶ መለስ በ5ኛው የፌዴራሊዝም ጉባዔ ላይ ተናግረዋል።

“የዘረጋንው ስርዓት በአዲስ ጋን የተጠመቀ የሰነበተ ጠጅ ሳይሆን፤ ከጥንስሱ ጀምሮ በአዲስ መልኩ የተሰራ ነው ብለዋል። ይሄም ፍጹም ባይሆን በፊት ከነበሩት በእጅጉ ይሻላል” ብለዋል አቶ መለስ።

XS
SM
MD
LG