በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካውያንና ዩክሬናውያን የቀዶ ሕክምና አጋርነት


የአሜሪካውያንና ዩክሬናውያን የቀዶ ሕክምና አጋርነት
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:32 0:00

አሜሪካውያን ሐኪሞች፣ ዩክሬናውያን የሞያ አጋሮቻቸው፣ ዐዲስ ቴክኖሎጂን በመላመድ፣ ውስብስብ የፊት ቀዶ ሕክምናዎችን እንዲያከናውኑ በማገዝ ላይ ናቸው።የኪይቭ ተወላጇ ኢቫንካ ኒቦር፣ በአሜሪካ፥ በጆሮ፣ አፍንጫ እና ጉሮሮ ሕክምና መስክ የሠለጠነች ሐኪም ናት።

ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ፣ አሜሪካውያን ሐኪሞችን በማስተባበር፣ “ፊት ለፊት”(FACE to FACE) የሚል ስም የሰጠችውን ተልዕኮ ጀመረች፡፡ በዚኽ ተልዕኮ የሚሳተፉ ሐኪሞች፣ ውስብስብ የፊት እና የአንገት ቀዶ ሕክምና ያከናውናሉ።

“አንዳንዶቹ ታካሚዎቻችን፥ የታችኛው መንጋጋቸው መጠገን አለበት፤ ከእግራቸው ወይም ከእጃቸው ላይ አጥንት ወስደን ነው የምንጠግነው። ይህ አጥንት፣ የደም ሥሮችን ይዟል፤ እናም በአንገት ዙሪያ ካሉ የደም ሥሮች ጋራ እናገናኘዋለን። በጣም ውስብስብ የኾነ፣ 15 ሰዓታትን የሚወስድ ቀዶ ሕክምና ነው፤” ብላለች ዶ/ር ኢቫንካ ኒቦር።

ዶር. ኢቫንካ ኒቦር፣ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው አሜሪካዊ አጋሮቿ ቀዶ ሕክምናውን በሚያደርጉበት ጊዜ ታግዛቸዋለች፤ እንዲሁም ለዩክሬን የሕክምና ባለሞያዎች የቪዲዮ ኮንፈረንስ ታዘጋጃለች፡፡

ማኖጅ አብርሃም የፊት ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሞያ ናቸው።

“በርካታ ጉዳቶችን እናያለን። አንድ ዐይናቸውን፣ አፍንጫቸውን ወይም መንጋጋቸውን ያጡ አሉ። በአንዳንድ የቀዶ ሕክምና ሥራዎች፣ ለምሳሌ፥ ጥቃቅን የደም ሥሮችንና ለታማሚ ብቻ የሚሠሩ የሰውነት ክፍሎችን በተመለከተ፣ እዚኽ ብዙ ልምድ የላቸውም። እኛ ያን ክፍተት ነው የምንሞላው። እዚኽ ያሉትን ሐኪሞች እናሠለጥናለን። የፊት ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሞያዎች፣ የዐይን ፕላስቲክ ቀዶ ሐኪሞች፣ የጭንቅላት እና የአንገት ቀዶ ሕክምና ሞያተኞች፣ እነዚኽ በሙሉ በጋራ ኾነን ሞያዊ እገዛ እናደርጋለን፤” ሲሉ፣ ዶ/ር ማኖጅ አብራሃም ስለ ሥራቸው አብራርተዋል።

ማኖጅ አብርሃም፣ በኒው ዮርክ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሞያ ሲኾኑ፣ 18 አባላት ያሉትና ሐኪሞች፣ ነርሶች እና የቴክኒክ ረዳቶች የተካተቱበት ቡድን አባል ናቸው።

ሠላሳ የሚኾኑና ፊታቸው ክፉኛ ለተጎዳ የዩክሬን ወታደሮች፣ ቀዶ ሕክምና አከናውነዋል።

ቭችስላቭ ኮንድራሾቭ፣ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው ወታደሮች አንዱ ነው።

“ሐኪሞችን ሳማክር፣ ሁሉም እንዳሉት፣ ‘የላይኛው ነርቭ ሞቷል፤ የታችኛው ግን ሊሠራ ይችል ይኾናል’ ብለውኛል። ዐይኔን መዝጋት እና መክፈት አልችልም። ፈገግ ማለት? አንድ ቀን ምናልባት፡፡ ነገር ግን፣ ሁሉም ነገር ሊሠራ እንደሚችል ተስፋ መኖሩን ይናገራሉ። ይህ በጣም ድንቅ ነገር ነው፤” ብሏል ቭችስላቭ ኮንድራሾቭ።

አሜሪካውያኑ የቀዶ ሕክምና ባለሞያዎች በአደረጉት አስተዋፅኦ፣ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ የዩክሬን ተዋጊዎች፥ ምግብ መብላት፣ መናገር፣ እንዲሁም መተንፈስ ችለዋል። ኢሊያ ስቭሮትስኪ፣ በጦርነቱ ያጣውን አፍንጫ መልሶ አግኝቷል።

“ጉዳት በደረሰብኝ ወቅት አፍንጫዬን አጣኹ። ሙሉ ለሙሉ። ቀድሞ የነበረኝን አፍንጫ አስመስለው ለመተካት እየሠሩ ነው። የሚችሉትን ኹሉ ያደርጋሉ። እስከ አሁን ስምንት ቀዶ ሕክምናዎችን አድርጌያለኹ።”

ዶር. ኢቫንካ ኒቦር፣ ዩክሬናውያን ሐኪሞች ስለሚያገኙት ልምድ ትናገራለች፤

“አጥንትን ለይተኽ ለማውጣት የምታደርገው ቀዶ ሕክምና፣ እንዲሁም እነዚኽን የደም ሥሮች ለይተኽ፣ ከዚያም ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት መልሰኽ፣ እያንዳንዱን አነስተኛ የደም ሥር እና ዋና የደም ማስተላለፊያዎችን በማጉሊያ መነጽር በመታገዝ መስፋት፥ የዩክሬን ሐኪሞች፣ ከአሜሪካዊ አጋሮቻችን የምንማረው ነገር መኾን አለበት፡፡”

በዩክሬናውያን ወታደሮች ፊት ላይ የሚታየው ጠባሳ፣ አገራቸውን በቅርቡ ነፃ ለማውጣት ተስፋ በማድረግ የከፈሉት ዋጋ ነው።

አሜሪካውያንና ዩክሬናውያን ሐኪሞች ደግሞ፣ ተጎጂ ወታደሮቹ፣ ፊታቸውን ሳይሸፍኑ መኖር እንዲችሉ፣ ማድረግ ያለባቸውንና የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው።

XS
SM
MD
LG