በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለኢትዮጵያ ምርጫ ውጤት የዩናይትድ ስቴትስ ንቁ አለመሆን አስተዋፅዖ ማበርከቱን አንድ አሜሪካዊ ምሁር ገለፁ


"በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይኖራል" ተብሎ ቀደም ሲል ተስፋ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም የታየው ግን የተጠበቀው አለመሆኑና የዩናይትድ ስቴትስ የተለሳለሰ አቋም አስተዋፅዖ ማበርከቱን በኦበርሊን ኮሌጅ የውጭ ፖሊሲና የአፍሪካ ጉዳዮች መምህር የሆኑት ኢቭ ሣንበርግ አስታውቀዋል፡፡

ሣንበርግ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ላይ ጊዜ ወስደው ከሚሠሩ ምሁራን አንዷ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ አማካሪ ሆነው በሠሩበት ጊዜ አይተዋታል፡፡

የአሁኑን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተሉ ይናገራሉ - ሣንበርግ፡፡ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ብሩህ እይታ፣ አስተዳደሩም ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መንገድ ይከፍታል የሚል ተስፋ እንደነበራቸውም አመልክተዋል፡፡ "ያ ግን አልሆነም" አሉ አሁን ያ ተስፋቸው የተሰረቀ በሚመስል አነጋገር፡፡

"የአሁኑ የኢትዮጵያ አመራር ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን አሣይቷል - ይላሉ ኢቭ ሣንበርግ - እነዚህ የዴሞክራሲ ሰዎች አይደሉም፡፡ የዴሞክራሲን ሂደት ረግጠዋል፡፡ የዴሞክራሲ ሂደት ሰዎች ወጥተው ድምፅ እንዲሰጡ ማድረግ ብቻ ሣይሆን በምርጫው ውስጥ በነፃነት የሚፎካከሩ ዕጩዎች መኖር ማለት ነው፡፡ ይህ አስተዳደር ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ፉክክር እንዳይኖር የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ስለዚህ እኔ ይህንን አስተዳደር እንደዴሞክራሲያዊ ልስለው አልችልም፡፡"

ምርጫውን እንዲህ ተስፋ የሚያስቆርጥ ገፅታ ያስያዘው ምን እንደሆነ ሣንበርግ ሲናገሩ አስተዳደሩ ብርቱ ተፎካካሪ እንዳይኖረው ከምርጫው በፊት የሚቻለውን ሁሉ ማድረጉን ያመለክታሉ፡፡

ሣንበርግ በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ፡- "ገዥው ፓርቲ ሕዝቡን አሸማቅቋል፤ የተቃዋሚ መሪዎችን እሥር ቤት አስገብቷል፤ መሪዎቹ ተሰድደዋል፤ አንዳንዶቹም ሥራቸውን ትተዋል፡፡ ለተቃዋሚ መሪዎች ይሠሩ የነበሩ ሰዎች ወከባ ደርሶባቸዋል፡፡ ግድያዎችም እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ ስለሆነም ይህ ምርጫ ይከታተሉት ለነበረና፤ የተሻለ ዴሞክራሲ ያለውና ይበልጥ ክፍት የሆነ የፖለቲካ ሂደት በኢትዮጵያ ይፈጠራል ብለው አስበው ለነበረ ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል፡፡"

ይህ ምርጫ በእርሣቸው እምነት እንዲህ ዴሞክራሲያዊነት የጎደለው ወደመሆን እንዲያመራ ካደረጉት ነገሮች መካከል ዩናይትድ ስቴትስ "ይጠበቅባት የነበረውን ያህል ንቁ አለመሆኗ"ና የኢትዮጵያ መንግሥት "ለታይታ ያወጣቸው የነበሩ አስመሣይ መግለጫዎች" መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ እንዲያ እንድትለሣለስ ካደረጓት ጉዳዮች መካከል እነዚያ አስመሣይ ያሏቸው መግለጫዎችና በአካባቢው ላይ ያሏት የደህንነት ጥቅሞች እንደሚገኙ ይጠቋቁማሉ፡፡ ከዚያ በላይ ግን ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲዋን ስትፈትሽ ኢትዮጵያ ያን ያህል የትኩረት ሥፍራ የተሰጣት አልነበረችም፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማም አሁን በቅርቡ ነው አዲስ የብሔራዊ ደኅንነት ስትራተጂ መንደፋቸውን ይፋ ያደረጉት፡፡

አሁን ግን ሁለቱ ሃገሮች በዚህ ምርጫ አያያዝና በውጤቱም ሣቢያ ወደ መካረር እየገቡ ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስም በ"ወዳጅዋ ምግባር" ደስተኛ አይደለችም፤ ኢትዮጵያም "ያላንቺ መኖር የምችል ነኝ" እየተባባሉ ነው፡፡ "ሁለቱም ወገኖች ግን ቆርጠው መቆራረጥን የሚፈልጉ አይመስለኝም" ይላሉ ኢቭ ሣንበርግ፡፡ ምክንያቱን ሲዘረዝሩም አንድም በእርዳታው፣ አንድም በደኅንነቱ - የኢትዮጵያም ጦር በአሜሪካ ሥልጠናና መሣሪያ የታጠቀ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በአካባቢው ባላት ቁልፍ መልክአ-ምድራዊና ፖለቲካዊ አሠፋፈር ሣቢያ አሜሪካም የምሥራቅ አፍሪካና የአደን ባሕረ ሠላጤ ደኅንነት የብሔራዊ ጥቅሟ ጉዳይ በመሆኑ ይፈላለጋሉ፡፡ "ተለያይተው አይለያዩም" ይላሉ ሣንበርግ፡፡

አክለውም "ኢትዮጵያ ለእርዳታ ፊቷን ወደሌሎች ኃይሎች ብታዞር ዩናይትድ ስቴትስ ምንና በምን መጠን እንደምታጣ ጠንቃቃ ግምገማ ማድረግ ይኖርባታል" ብለዋል፡፡

"አሁን ባለው ሁኔታ ታዲያ የዩናይትድ ስቴትስም ጫና ሆነ የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎች ቡድን ነቀፌታ እነርሱ የሚፈልጉትን ውጤት አያስገኝም ማለት ነው?" ተብለው ሲጠየቁ ምንም እንኳ አሁን በእጃቸው የተጨበጠ መረጃ ባይኖራቸውም "እጅግ አስፈላጊ የሆነው ዲፕሎማሲ የሚከናወነው ከዕይታ ውጭ ነው" ብለዋል፡፡

በማንኛውም መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንደሚመጣና የዴሞክራሲ ግንባታ ተስፋ እንዳለ ፕሮፌሰር ኢቭ ሣንበርግ እንደሚያምኑ ቢናገሩም አሁን ባለው የኢትዮጵያ አሠራር ውስጥ ግን ይህ ይገኛል ማለት ዘበት ነው ይላሉ፡፡

በኢሕአዴግ በራሱ ውስጥም ይሁን ወደፊት ሊፈጠር በሚችል ኅብረት ይህንን የዴሞክራሲ ሣንበርግ የሚሰጡት ለመጭው ትውልድ ነው፡፡

XS
SM
MD
LG