ከአጋሮች ጋራ በመኾን በኢትዮጵያ ለተፈናቃዮች የሚውል ድጋፍ ይፋ ያደረገው የአውሮፓ ኅብረት፣ ዜጎችን ለመፈናቀል እና ለሠቆቃ የዳረጉ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት እና አጋሮቹ፣ በግጭቶች እና በተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና የአስተናጋጅ ማኅበረሰቦችን የኑሮ ኹኔታ ለማሻሻል ይውላል የተባለ የ43ነጥብ5 ሚሊዮን ዩሮ(የ2ነጥብ7 ቢሊዮን ብር) ድጋፍ፣ ዛሬ ዐርብ፣ ግንቦት 9 ቀን ይፋ አድርገዋል፡፡
ይኸው የሦስት ዓመት የድጋፍ መርሐ ግብር፣ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች ማለትም አፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ትግራይ እንደሚተገበር፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት፣ አራቱ ክልሎች የተመረጡበትን ምክንያት አስረድተዋል። በዋናነት በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የተካሔደው ጦርነት፣ አሁንም በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት ምክንያት አካባቢዎቹ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አንሥተዋል፡፡
በክልሎቹ እየተደረገ እንዳለ በገለጹት ድጋፍም፣ 200ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በጤና ተቋማት አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ያስታወቁት አምባሳደሩ፣ ከሰባት ሺሕ በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚያገኙ አመልክተዋል፡፡ በመኾኑም፣ “በጣም የተጎዱትን ሰዎች አነስተኛ ሥራዎችን እንዲጀምሩና ወደ መደበኛው ማኅበረሰብ እንዲቀላቀሉ በማድረግ፣ ከጦርነቱ ጉዳት እንዲያገግሙና ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ እየሞከርን ነው፤” ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ 4ነጥብ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ፣ በሌሎች ክልሎች ያሉ ተፈናቃዮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሐ ግብርም ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡
የሶማሌ፣ ደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚረዱባቸው ሌሎች ፕሮግራሞችም መኖራቸውን ያመለከቱት አምባሳደሩ፣ “ኹሉም የተፈናቀሉ ዜጎች ተጠቃሚ በሚኾኑበት ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ መንገድ ለመተግበር እየሞከርን ነው፤” ብለዋል፡፡
በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች የተቸገሩ ሰዎችን ለመድረስ የማይቻልበት አስቸጋሪ ኹኔታ መኖሩን የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የኾኑ ግጭቶች እንዲቆሙና ለሰብአዊ ድጋፍ አመቺ ኹኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል፡፡
ብዙ ተፈናቃዮችንና ተጨማሪ ፍላጎቶችን እየፈጠረ ያለ ግጭት እየቀጠለ ባለበት ወቅት፣ የቀደሙ ግጭቶች ያስከተሉትን ጉዳት ለመቀነስ መሞከር “ማብቂያ የሌለው ታሪክ ኾኖ ይቀጥላል” ሲሉም ግጭቶች እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ባለሥልጣናት፣ ለለጋሽ ድርጅቶች እና ለፈጻሚ አካላት ሥራ ምቹ ኹኔታን እንዲፈጥሩም አመልክተዋል፡፡
መንግሥት እና የታጠቁ ቡድኖች ግጭቶችን በሰላም መፍታት እንዳለባቸው፣ አምባሳደሩ በአጽንዖት አንሥተዋል፡፡ ግጭቶች እንዲቆሙና ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ ንግግር እና ድርድር እንዲደረግ፣ ላለፉት ዓመታት ያለማቋረጥ ጥሪ ማቅረባቸውን
አውስተው፣ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ለሀገር ብቻ ሳይኾን በዋናነት ለሕዝቡም ጭምር የተሻለና ዘላቂ ውጤት ያመጣሉ ብለው በእጅጉ እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ “በእነዚኽ ሦስት ዓመታት ጾታን መሠረት ያደረጉትን ጨምሮ ብዙ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ኢትዮጵያ ከዚኽ የተሻለ ነገር ይገባታል፤” ሲሉ አክለዋል፡፡
ግጭቶች በሰላም ውይይት እንዲፈቱ ሌሎች አካላትም ጥሪ ማቅረባቸውን መቀጠላቸው ይታወቃል፡፡ ይኹን እንጂ፣ “ለሰላማዊ ንግግር በሬ ክፍት ነው” የሚለው መንግሥት፣ ታጣቂ ቡድኖችን ለሰላም ዝግጁ እንዳልኾኑ በመግለጽ ይከሳል፡፡ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በበኩላቸው፣ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋም፣ አገራቸው የቀጠሉ ግጭቶችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ በአንጸባረቀው ያለፈው ሳምንት ንግግራቸው፣ “በኢትዮጵያ በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላት፣ ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ፣ በንግግር ሰላም እንዲያሰፍኑና የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ” ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡
የአምባሳደሩን የፖሊሲ ንግግር፣ “በሚገባ ያልተጤነ” ሲል የነቀፈው የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ፣ በመግለጫቸው፣ “መሠረት የሌላቸውን ክሶች በመንግሥት ላይ አሰምተዋል፤ አገራችንን በምን መልክ ማስተዳደር እንደሚሻለንም ምክር ለመለገስ ሞክረዋል፤” ሲል መቃወሙ ይታወቃል፡፡
መድረክ / ፎረም