ኢሕአዴግ ወደ መንበረ ሥልጣኑ ከወጣ ወዲህ ባለፉ ዓመታት ሁሉ ለኢትዮጽያ የማዝገሟም ሆነ የመፍጠኗ፣ የመስማማቷም ሆነ የመለያየቷ፣ የጥንካሬዋም ሆነ የድክመቷ መንስዔዎች ሁሉ ምንጫቸው የፓርቲያቸውም ይሁን የራሣቸው አዕምሮ ያፈለቋቸው መለስ ዜናዊ የቀየዷቸውና ተግባር ላይ ያዋሏቸው ፖሊሲዎቻቸው ናቸው፡፡
ኢሕአዴግ ዛሬ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ ከድርጅቱ ልደት እስከእራሣቸው ሕልፈት “በበሣል አመራራቸው” ይዘውት መጓዛቸውን ጠቅሷል፡፡ እርሣቸው የተለሟቸውንና ያራመዷቸውን መርሆችና ፖሊሲዎች፣ ራዕያቸውንም ይዞ እንደሚቀጥል ፓርቲያቸውም የሚኒስትሮቹ ምክር ቤትም አስታውቀዋል፡፡
መለስ ዜናዊ የጊዜያዊ መንግሥቱ መሪ ሆነው በ1983 ዓ.ም ወደ መንበረ ሥልጣኑ በዘለቁ ጊዜ፣ ከዚያ በፊት፣ በበረሃ ትግላቸው ዘመን፣ በኋላም ርዐሰ-ብሔርም፣ መራሂ መንግሥትም ሆነው የዘለቁበትና ፓርቲያቸውም የሚያራምደው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አስተሣሰብ እና የኢትዮጵያ በጎሣ ላይ የተመሠረተ ፌደራላዊ አደረጃጀት በቀዳሚነት ይነሣል፡፡
በአንድ ወገን ያሉ ተቃዋሚዎችና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኞች ይህ አስተሣሰብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ወደመከፋፈልና ወደመበታተን የሚወስድ አድርገው ሲያነሱ ሌሎች ደግሞ በድጋፉ ወገን የቆሙ “የለም፣ የሕዝቦቿን እኩልነት ያስጠበቀ፣ ለሃገሪቱም ዘላቂ ሕልውና ዋስትናን የሰጠ ነው” ሲሉ ይሟገታሉ፡፡
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡