መንግሥት በሁከቱ ሰማያዊ ፓርቲና ግንቦት ሰባትን ይከስሳል
ሰማያዊ ፓርቲ ክሡን አስተባብሏል፡፡ አርበኞች-ግንቦት ሰባት ግንባር በሰልፈኞቹ ላይ የተፈፀመውን ድብደባ አውግዟል፡፡ “ይህንን ሥርዓት ለማስወገድ የሚካሄድን ማንኛውንም እንቅስቃሴ እንደግፋለን” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ ጠርቶት በነበረው ፀረ-አይሲል ትዕይንተ-ሕዝብ ላይ ሁከትና ብጥብጥ የቀሰቀሱት ግንቦት ሰባትና ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው ሲሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሰሱ።
የኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ትናንት ምሽት ላይ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን፤ ዛሬ ደግሞ የአዲስ አባባ የፌዴራል ፖሊስ ኮማንድ ፖስት መግለጫ ግንቦት ሰባትና ሰማያዊ ፓርቲ ከብጥብጡ በስተጀርባ አሉ ብሏል።
ያልተፈቀደ ሠልፍ ለማድረግ በመዘጋጀትም መንግሥት ሰማያዊ ፓርቲን ከስሷል የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፓርቲአቸው ግጭቱን እንዳልቀሰቀሰ፣ ከግንቦት ሰባት ጋርም ምንም ግንኙነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
ይልቁንም መንግሥት ለመጭው የግንቦት ምርጫ ውድድር የተመዘገቡትን ጨምር ብዙ የፓርቲውን አባላት እንዳሠረ ተናግረዋል።
የግንቦት ሰባት መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋም ለቪኦኤ በሰጡት ምላሽ እንዲህ ዓይነቱ ውንጀላ የአምባገነኖች ልማድ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ በምርጫ ሥልጣን ልንይዝ እንችላለን በሚል ሰላማዊ ትግል ከመረጡ ድርጅቶች ጋር ግንባራቸው አርበኞች - ግንቦት ሰባት አንዳችም ግንኙነት እንደሌለው ዶ/ር ብርሃኑ አመልክተው ይሁን እንጂ ሥርዓቱን ለማስወገድ ሃገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱትን ማንኛቸውንም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ቢኖሩበትም ባይኖሩበትም እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡
ሊብያ ውስጥ የኢትዮጵያዊያኑ የዛሬ ውሎ ምን ይመስል እንደነበረ ይዘናል፤ ከተገደሉት ኢትዮጵያዊያን መካከል የአንዱን ቤተሰብ አነጋግረናል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬም ኀዘን ላይ ነች፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡