በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ክረምቱ ጨርሶ እስኪወጣ ጥንቃቄው መቀጠል እንዳለበት የሚቲኦሮሎጂ ባለሥልጣን አሣሰቡ፡፡


የአሁኑ ክረምት የሚወጣበት ጊዜ ከመስከረም ሁለተኛ አጋማሽ እስከ ኅዳር እንደየአካባቢውና የአየር ንብረት ሁኔታው ስለሚራዘም ሰዎች እና ተቋማት ሥራቸውን ሲያቅዱና ሲያከናውኑ የዝናቡን እና ተያያዥ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲኦሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪዳኔ አሰፋ አሳስበዋል፡፡

የክረምቱን ወቅትና እየጣለ ያለውን ከባድ ዝናብ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ያስከተላቸውን ጉዳቶች መሠረት አድርገን ሁኔታውን እንዲያብራሩልንና ወደፊት የሚመጡት ወራት ምን ገፅታ እንደሚኖራቸው እንዲጠቁሙን ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሚቲኦሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ባለፈ ዝግጅታችን ስለዝናቡ አጠቃላይ ሁኔታና ሥርጭት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ስላሉት አደጋዎችና ከእነርሱ ለመዳን ወይም ለማምለጥ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችና እርምጃዎች በዝግጅቱ ያለፈ ክፍል ተናግረው ነበር፡፡

በዚህ የቃለ ምልልሱ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ የክረምቱ መውጫ እና መጭው የአየር ሁኔታ ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል አቶ ኪዳኔ አሰፋ ሲናገሩ ቀደም ሲል በተተነበየው መሠረት የዝናቡ ሁኔታ መደበኛና በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ከመደበኛ በላይ እንደሚሆንና ክረምቱ ሲጀምርና በማብቂያውም ላይ በየአካባቢው መደበኛ ፈር የተከተለ እንደሚሆን ቀደም ሲል ተተንብዮ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ክረምቱ በመስከረም ሁለተኛ አጋማሽ ከሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎች መውጣት እንደሚጀምርና ከዚያም ወደ ደቡብ ምዕራብ እስከ ሕዳር እንደሚዘገይ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲው ዳይረክተር ጠቁመው ክብደቱም እንደየአካባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ሊለያይ ስለሚችል ወቅቱ ሙሉ በሙሉ እስኪያበቃ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ማንኛውም ሰው እና ተቋም፣ በግንባታ፣ በመንገድ ሥራዎችና በቤቶች ሕነፃ ላይ ያሉ ሁሉ የወቅቱን ሁኔታ አገናዝበው ማቀድና መንቀሣቀስ ይገባቸዋል ብለዋል አቶ ኪዳኔ አሰፋ፡፡

የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ሁኔታውን በውኃ ኃብት ሚኒስቴር ሰብሳቢነት የሚመራ የኤሌክትሪክ ኃይልና የሚቲኦሮሎጂ መሥሪያ ቤቶች በአባልነት የሚገኙበት ግብረኃይል በቅርብ እየተከታተለ መሆኑንም አቶ ኪዳኔ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃዎች ጥራታቸውና ተዓማኒነታቸው እየተሻሻለ የመጣ በመሆኑ ሰዉ ትክክለኛነታቸውን አምኖ ሊጠቀምባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዚህ ዓመት ከዝናብ ጋር የተያያዘ የምግብ እጥረት ያጋጥማል ብለው እንደማያስቡም አቶ ኪዳኔ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG