በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በተመድ ንግግራቸው ማህበራዊ መገናኛን ተቹ


የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ

የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን የተሳሳተ መረጃን በማዳረስና ጽንፍ የረገጡ ቡድኖችን የጥላቻ ንግግር እያስፋፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ትላንት ባደረጉት ንግግር አሳሰቡ።

የአየር ንብረት ለውጥ በድርቅና ጎርፍ አደጋዎች የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተነ መሆኑን አቶ ሀይለማርያም በንግግራቸው አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጊዜ ሳያጠፉ የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ያላቸውን ትችት በንግግራቸው ዳሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የዓለም ሰላምና መረጋጋት በግጭቶችና ጦርነቶች፤ እንዲሁም በማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን የህዝብ ተቆርቋሪ እንደሆኑ የሚገልጹ ቡድኖች በአቶ ሃይለማርያም እይታ ጽንፍ የረገጡ አካላት ሁከትን እየቀሰቀሱ እንደሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄንን ንግግር ያሰሙት ሀገራቸው ላለፉት በርካታ ወራት በተለይ በማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች የሚሰራጩባቸው ህዝባዊ ተቃውሞዎች እየታመሰች ባለበት ወቅት ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በጥይት ተኩሰው እንደገደሉ የመብት ድርጅቶች ሲያስገነዝቡ ቆይተዋል። በኦሮሚያ አንደኛ አመቱን ሊያስቆጥር የተቃረበ ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች፣ በተለያዩ ወቅቶች ሲካሄድ ቆይቷል። በአማራ ክልል በተለይ ወልቃይት፣ ጎንደርና ጎጃም ህዝባዊ እምቢታ እየተስፋፋ መጥቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃንን በማፈን የጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ተቆርቋሪ ድርጅቶች የሚተቿት ሀገር ናት። በማህበረሰብ የመገናኝ ብዙሃን "ህገመንግስቱ ይከበር" በሚል ዘመቻ ያካሄዱ የዞን ዘጠኝ ጸሃፊዎችና ሶስት ጋዜጠኞች ለበርካታ ወራት በሽብር ወንጀል ተከሰው የታሰሩባትም ሀገር ናት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በመንግስታቱ ድርጅት ንግግራቸው በጥቅሉ፤ ዝርዝር ወይንም አንድን ሀገር ሳይለዩ፤ መልካም ግንኙነት ያለን ሀገሮች ሁከት ቀስቃሽ ግለሰቦችና ቡድኖች አስጠልለዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለመንግስታቱ ድርጅት ባሰሙት ንግግር ኢትዮጵያ ዘለቄታ ያለው ልማት ለማምጣት ከአጋር ድርጅቶችና ከህዝቧ ጋር የያዘችውን የእድገትን ጉዞ በዝርዝር ሲያስረዱ፤ እመርታዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል። ሆኖም የአከባቢ አየር ለውጥ እያስከተላቸው ያሉ ድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች አሁንም ከድህነት ለመውጣት የሚታገሉ ህዝቦችን ወደኃላ እያስቀሩ ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ የመሩት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተለይ ማክሰኞ እለት የዩናይትድ ስቴይትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በስደተኞችና ፍልሰተኞች ዙሪያ ባካሄዱት ጉባዔ ዋና አጋር ሆኖ ሰርቷል።

የተመድ ጉባዔ- ኒውዮርክ
የተመድ ጉባዔ- ኒውዮርክ

በ192 የተ.መ.ድ አባል ሀገሮች የተፈረመው የፍልሰተኞችና ስደተኞች ስምምነት ላይ እያንዳንዱ ሃገር ድርሻውን ለመወጣትና ሥራ ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጿል።

የኒውዮርኩ ስምምነት ምእራባዊያን መንግስታትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን ለሚያስጠልሉ፤ ፍልስተኞችን ደግሞ በፈቃዳቸው ወደ ሀገራቸው በመመለሱ ስራ ለሚተባበሩ ሀገሮች የገንዘብና የምግብ እርዳታ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል።

ኢትዮጵያ ከብርታንያ የ80 ሚሊዮን ፓውንድ እገዛ እንደምታገኝ ተገልጿል። አላማውም በኢትዮጵያ ለኤርትራዊያን ስደተኞችና ፍልሰተኞች የሥራ እድል መፍጠርና መልሶ ማቋቋም እንደሆነ ተረድተናል። ጉዳዮ እንዴት እንደሚተገበር ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጠይቀን ምላሻቸውን እናቀርባለን።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለተመድ ባሰሙት ንግግር የማህበረሰብ መገናኛን ተችተዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:30 0:00

XS
SM
MD
LG