ቦይንግ 737 ማክስ-8 ጄት አይሮፕላኑ ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ለመብረር ከተነሳ 6 ደቂቃዎች በኋላ በመከስከሱ ህይወታቸውን ላጡት ተሳፋሪዎች ብሄራዊ የሀዘን ቀን ታውጆ ውሏል።
ቢያንስ 29 የሚሆኑ ተሳፋሪዎች ናይሮቢ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አለም አቀፍ ዋና ጽህፈት ቤቶች በሚደረግ የአከባቢ ጥራት አመታዊ ጉባኤ ላይ ለመስተፍ ይጓዙ እንደነበር ታውቋል። ልዑካኑ ዛሬ በስብሰባው ቦታ ሲደርሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰንደቃላማ ዝቅ ብሎ ተሰቅሎ ነበር።
በናይሮቢው ስብሰባና ኒው ዮርክ የተደረገው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ሲከፈቱ ሙታኑ በአንዳፍታ ዝምታ ታስበዋል።
“ትልቅ አለም አቀፍ ሃዘን ገጥማናል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሀዘን ተዋህዷል። ለሙታኑ ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ ለኢትዮጵያ ማንግስትና ለህዝቧ፣ እንዲሁም በአስከፊው አደጋ ለተጎዱት ሁሉ ጽኑ ሃዘኔን እገልጻለሁ” ሲሉ የድርጅቱ ዋን ፀሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ ኒው ዮርክ ላይ የሀዘን መልእክት አስተላልፈዋል።
ከአደጋው በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 ጄት አይሮፕላኖች እንዳይበሩ አግዷል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ