የኢትዮጵያ ፌደራል ኃይሎች ዛሬ ከሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ጋር ጂግጂጋ ላይ መጋጨታቸውና በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የክልሉን የተወሰኑ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር ለማዋል መንቀሳቀሳቸውን የሶማሊኛ ዝግጅት ክፍላችን ዘግቧል።
ፌደራሉ የመከላከያ ኃይል ወደ ጂግጂጋ የገባው ትናንት ዐርብ ምሽት እንደነበረና ዛሬ ማለዳ ላይ ቁልፍ የሚባሉ ይዞታዎችን ተቆጣጥሮ የክልሉን ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሐመድ ኦማርን (“አብዲ ኢሌ” ተብለውም ይጠራሉ) ቢሮ፣ የክልሉን ምክር ቤት ሕንፃና ሌሎችም የመንግሥት ተቋማትን መክበቡን ዘገባው አመልክቷል።
ጦሩ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ከክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል ጋር ለአጭር ጉዜ የተኩስ ልውውጥ መከፈቱንና በዚያ ወቅት ከተማዪቱ ውስጥ ረብሻ መፈጠሩን በርካታ እማኞችን የጠቀሰው ይኸው የቪኦኤ የሶማሊኛ ዝግጅት ክፍል ዘገባ አጋጣሚውን የተጠቀሙ ሰዎች ጎዳና ላይ መውጣታቸውን፣ ዝርፊያ መፈፀማቸውንና ሕንፃዎችን ማቃጠላቸውን ገልጿል።
የተቃጠሉትና የተዘረፉት የሶማሌ ብሄረሰብ አባል ያልሆኑ የሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሱቆችና ንብረቶች መሆናቸውን የጠቆመው ይኸው ዘገባ አንዲት የኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስትያንም መቃጠሏን አመልክቷል።
የክልሉ ባለሥልጣናትና የሃገር ሽማግሌዎች የፌደራሉን መንግሥት እርምጃ መቃወማቸው የተገለፀ ሲሆን የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ማምሻውን ባወጣው መግለጫ “ሶማሌ ክልል ውስጥ የሽግግር ለውጥ መምጣት ያለበት ኦብነግን፣ ፌደራል መንግሥቱንና ሌሎችም አግባብ ያላቸውን ወገኖች ባካተተ ሰላማዊ ድርድር ብቻ መሆን እንዳለበት” አሳስቦ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አሰምቷል።
ኦብነግ አክሎ “ኦጋዴን ውስጥ የሚገኘው የሶማሌ ሕዝብ መብቶቹን ለማስከበር እንዲቆምና ‘የውጭ ኃይሎች’ ስለዕጣ ፈንታው እንዲወስኑ እንዳይፈቅድ” ጠይቆ “የእምነት ተቋማትና የሲቪሎች ንብረቶች አጋጣውን ለመጠቀም በሚፈልጉ ግለሰቦች ለጥቃት እንዳይጋለጡ እንዲከላከል” አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስቴር ልኮልኛል” ባለው መግለጫ “በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ” ሚኒስቴሩ ማስታወቁን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።
“ዛሬ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ ውስጥ የተከሰተው ብጥብጥ፣ ቀጥሎም ወደ ሌሎች አንዳንድ የክልሉ ከተሞች የተዛመተው ሁከት በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ሊገታና ሊታረም የሚገባው ድርጊት ነው” ሲል የመከላከያ ሚኒስቴር ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል።
መግለጫው አክሎም “የመከላከያ ሠራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የተከሰተውን ሁከት በቅርብ እየተከተተለና ሁኔታውን ለመቆጣጠርና ኅብረተሰቡን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ብጥብጡ በተፈለገው ፍጥነት ሊቆም እንዳልቻለ” መግለፁን ዘገባው አሥፍሯል።
“የክልሉ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት አደጋ ውስጥ እየገባ” መሆኑን ያስታወቀው ይኸው የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ “የመከላከያ ኃይሉ ሁከትና ብጥብጡን በዝምታ እንደማይመለከት፣ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ በጥብቅ እንደሚያሳስብ” አስገንዝቧል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ