በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ሞያተኞች እሮሮ


በእናቶች ሞት ቅነሳ ከፍተኛ አስተዋፆ ካበረከቱ በኋላ ሞያቸውንና ራሳቸውን ለማሳደግ የሚችሉበት ከፍተኛ ትምሕርት እንዳያገኙ መከልከላቸውን፣ ይህን ለማድረግ የሚያችል የትምሕርት ክፍል እንደሌለም በኢትዮጵያ የተቀናጀ ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ሞያተኞች ገለጹ። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መሥሪያቤት ሚኒስትሮች በተቀያየሩ ቁጥር የተገባላቸው ቃል እንደታጠፈም ተናግረዋል። “ታማኝ አገልጋይ ብቻ ተደርገን የተተውን ሰዎችን ነን”ሲሉም አማረዋል።

በኢትዮጵያ የድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ሞያተኞች እሮሮ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:33 0:00

አቶ መለስ ታከለ በኢትዮጵያ የተቀናጀ ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ሞያተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ናቸው። ወደ ሞያው የገቡት በ2001 ዓ.ም በቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በተነደፈ ፕሮግራም አማካኝነት እንደሆነ ይናገራሉ።

የእናቶች ሞት ቁጥር በኢትዮጵያ ከፍተኛ መሆን በዓለም ተጠቃሽ አድርጓት በነበረ ጊዜ የተጀመረ ፕሮግራሙ ነው። በወቅቱ የእናቶች ሞት በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የሰለጠኑ ባለሞያዎች ገጠር ተመድበው እንዲሠሩ ለማድረግ እጥረት በመኖሩ በመጀምሪያ ዲግሪ የተማሩ የጤና መኮንኖችን በሦስት ዓመት ተጨማሪ ትምሕርት በሁለተኛ ዲግሪ እንዲመረቁ መደረጉን አቶ መለስ ይናገራሉ። እርሳቸውም በዚህ መሰረት ተምረው የድንገተኛ ቀዶ ጥገና ባለሞያ እንደሆኑ ይገልፃሉ።

ነገር ግን ይላሉ ቅሬታቸውን ሲጀምሩ "አንዴ ሥራውን ከጀመርን በኋላ በትምሕርት ሞያችንን ልናሳድግበት የምንችልበት መንገድ ዝግ ሆነብን" ብለዋል።

አቶ መለስ በዚህ ሞያ የሰለጠኑ ባለሞያዎች ቁጥር 680 እንደሚደር ገልፀው እርሳቸው በሚመሩት ማኅበር ውስጥ ወደ 350 የሚሆኑት የተመዘገቡ ባለሞያዎች እንደሚገኙ ይናገራሉ። “ቅሬታውም የሁሉንም ባለሞያዎች ይወክላል” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን በደሌ ሆስፒታል ውስጥ የድንገተኛ ቀዶ ጥገና ባለሞያ የሆኑት አቶ አለማየሁ አበእግዜር “በያለንበት ቦታ ለሕዝብ ያበረከትነው አስተዋፆ ከፍተኛ ነው።” ይላሉ።

አቶ አለማየሁ በወቅቱ የነበሩት ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በቀጣይ አዲስ ሥርዓተ ትምሕርት ተቀርፆ ትምሕርታቸውን የሚቀጥሉበት ዕድል እንደሚፈጠር ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ቃላቸውን ሳይፈፀሙ መሥሪያ ቤት መቀየራቸውን ያስታውሳሉ።

ባለሞያዎቹ እንደሚሉት ጉዳዩ ውይይት ተደርጎበት ሥርዓተ ትምሕርት እንደሚቀረፅና ወደ ሕክምና ዶክተር የሚሻገሩበት የትምሕርት ዕድል የሚፈጠርበት መንገድ በባለሞያዎች ጥናት ተደርጎበት ወደ ሥራ ሊገባ ሲል እንደገና ሚኒስትሩ በመቀየራቸው መቋረጡን ይናገራሉ።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ መለስ ጥያቄያቸው ትምሕርት ብቻ እንዳልነበር ይናገራሉ። በትግራይ ክልል ኮረም ከተማ ኮረም ሆስፒታል ውስጥ ባለሞያ የሆኑት አቶ ቱማይ አብርሃ ቅሬታቸንን ይዘው ያልሄዱበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት እንደሌለ ይናገራሉ።" የትምሕርት ዕድል ከመነፈጋችን በተጨማሪ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም ቀርተውብናል" ባይ ናቸው።

በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በሌ ሆስፒታል ባለሞያ የሆኑት አቶ አብርሃም ዶረና፤ " ከሰብዓዊ መብቶች አንዱ የሆነው የመማር መብት ተነፍገናል" ብለዋል።

ባለሞያዎቹ እነርሱ ሲማሩ ትምሕርቱ ይሰጥ የነበርው በሦስት ዩኒቨርስቲ እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን በዐስራ አንድ ዩኒቨርስቲዎች በመሰጠት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ሁኔታውን የሚያውቁትም ኃላፊዎች ሆነ አሁን ያሉና የዜጎች ጉዳይ ያሳስበናል የሚሉ ሁሉ ምላሽ እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ።

“አንድ ባለሞያ ያለ ምንም መሻሻል ዕድሜውን ሙሉ አንድ ቦታና አንድ ሞያ ላይ እንዲሠራ እንዴት ይገደዳል?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

የባለሞያዎቹን ጥያቄ ይዘን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌስር ይፍሩ ብርሃን፣ ሚኒስትር ዴታ ዶ/ር አሚር አማንና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰው ሃይል ሃብት ዳይርክቶሬት ዳይርክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የእጅ ስልኮች ላይ ለተደጋጋሚ ቀናት ሙከራ አድርገን ነበር ሁሉንም ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖብናል። ነገር ግን ሙከራችንን እንቀጥላለን ምላሻቸውንም እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG