በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ግሽበት ንረት ተመን ቁጥጥር


የኢትዮጵያ ዓመታዊ የግሽበት መጠን ባለፈው ታኅሣስ ውስጥ በ14 ነጥብ 5 ከመቶ ማሻቀቡ ተዘግቧል፡፡

ይህ የሆነው ደግሞ በብር የምንዛሪ አቅም ላይ በተደረገው ቅነሣ ምክንያት በተለይ የምግብ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት መሆኑ ተሰምቷል፡፡

አዲሱ የዋጋ ተመን ቁጥጥር ምናልባት የዋጋውን ውድነት ሳያረግበው እንደማይቀር መንግሥት ተስፋ እንዳለው የአሜሪካ ድምፁ ዘጋቢ ፒተር ሃይንላይን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው ዘገባ አመልክቷል፡፡

የግሽበቱ መጠን በኅዳር ከነበረበት 10.2 ከመቶ በታኅሣስ ወደ 14.5 ከመቶ ማሻቀቡን የጠቆመው ማዕከላዊው የስታቲስቲክስ መሥሪያ ቤቷ ባለፈው ሣምንት ባወጣው መረጃ ነው፡፡

በኤጀንሲው መግለጫ መሠረት የምግብ አቅርቦቶች ዋጋ ወደ ዘጠኝ ከመቶ፣ ምግብ ያልሆኑ ሸቀጣሸቀጥ ደግሞ ወደ 23 ከመቶ በሚጠጋ መጠን አድጓል፡፡

መንግሥት ባለፈው መስከረም በወሰደው የብር የምንዛሪ አቅም ማስተካከያ እርምጃ የዶላርን ምንዛሪ በ17 ከመቶ ካሣደገ ወዲህ ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የዋጋው መጠን በእጅጉ ንሯል፡፡

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ የንግድ አለመመጣጠን ከፍተኛ እንደነበረና ወደ 5.8 ቢልዮን ዶላር የንግድ ጉድለት እንደተመዘገበ ታውቋል፡፡ ይህ ጉድለት የሚታየው 1.2 ቢልዮን ዶላር በሚያስገኝላት ወጭ ንግዷ እና 7 ቢልዮን ዶላር በሚያስወጣት ገቢ ንግዷ መካከል ነው፡፡

በምግቡና በእህል ገበያ ላይ የሚታየው ዋጋ እጅግ በመናሩ ምክንያት መንግሥት በወዲያኛው ሣምንት በበርካታ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመንና ቁጥጥር ጀምሯል፡፡

በዳቦ፣ በሥጋ፣ በስኳር፣ በመጠጦችና በምግብ ዘይት ላይ የተጣለው ጣሪያ እንዲሁም እዚህ ግባ የማይባል የተዳከመ ገቢ ያለውን ሸማች በብዙ ያስደሰተ መሆኑ ቢነገርም በሌላ በኩል ደግሞ ትርፋቸው አብዝቶ ተጎድቶባቸዋል የተባሉ አቅራቢዎችና ቸርቻሪዎችን ቅር እንዳሰኘና እንዳበሣጨ ይሰማል፡፡ (የኢትዮጵያ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በዓመት ከ400 የአሜሪካ ዶላር በታች ነው፡፡)

አንዳንድ ነጋዴዎች 'እንድሸጥ እየተገደድን ያለነው ሸቀጦቹን ካስገባንበት ባነሰ ዋጋ ነው' እያሉ ቅሬታቸውን በይፋ ይናገራሉ፡፡

ባለፈው ሣምንት ውስጥ ከተመን በላይ ሲሸጡ የተገሁነ ከመቶ በላይ ቸርቻሪዎችን ሱቆች መንግሥት መዝጋቱን የዜና ምንጮችና ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የዋጋ ተመን ጥሰቶች ከተደጋገሙ ደግሞ ለከባድ ቅጣትና ለእሥርም ሊዳርጉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የዋጋ ቁጥጥር 'የገበያውን ሥርዓት ያዛባል' ሲሉ ተቃዋሚዎችና የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ መሆናቸው ይሰማል፡፡ 'እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በተደጋጋሚ ተሞክሮ ፍሬያማ ሳይሆን ቀርቷል፤ ምርታማነትንም ያደናቅፋል' ይላሉ፡፡

''በመንግሥት ስህተት የንግዱን ማኅበረሰብ መወንጀልና መክሰስ አግባብ አይደለም'' ይላሉ ጡረታ ላይ ያሉት የሕግ ባለሙያና የቀድሞ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ቡልቻ ደመቅሣ፡፡

''እኔ በቸርቻሪዎቹና በነጋዴዎቹ አላዝንም፤ ይልቅ የማዝነው ዋጋን በመቆጣጠር ጉልበቱ በሚመካው መንግሥት ነው፡፡ ዋጋዎችን ልትቆጣጠራቸው አትችልም፤ በዓለም ውስጥ በየአካባቢው ተሞክሮ አልተቻለም፣ ውጤት አላስገኘም፡፡ ጨርሶውኑ አምባገነናዊ ኅብረተሰብ መፍጠርህ ካልሆነ በስተቀር ዋጋን ተቆጣጥሮ ማቆም አይቻልም፡፡'' ብለዋል አቶ ቡልቻ ደመቅሣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየታቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሸማቾች ይህንን የዋጋ ጣሪያ ተመን በስፋት የደገፉት መሆኑ ይነገራል፡፡ ሸንቁጥ ተሾመ ሸማች ናቸው፡፡ የሰዉ ገቢ እጅግ በመመናመኑ ምክንያት ለቀለቡ የሚያወጣውም እያጠረ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ አቶ ሸንቁጥ ከአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ጋር ሲወያዩ እንዲህ አሉ፡- "መንግሥት የዋጋ ቁጥጥር ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በነፃው ገበያ ሁሉም እንደፈለገው ዋጋውን ይጨምራል፤ ሰዉ በዚህ ምክንያት መግዛት ይሣነዋል፡፡ በመጨረሻም የሚሸመት ይጠፋል፡፡ የሃገሪቱ ኢኮኖሚና ሕዝቡ እንደፈለጉ ሊያወጡ የሚያስችላቸው አቅም የላቸውም፡፡ በመሆኑም ዋጋውን የማትቆጣጠር ከሆነ ሰዉ ለቸነፈር ይጋለጣል፡፡"

የንግድ ሚኒስቴር በሌሎችም አቅርቦቶች ላይ ቁጥጥሩን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው አንድ ባለሥልጣኑ ባለፈው ሣምንት ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በያዘው የአምስት ዓመት የምጣኔ ኃብት ዕቅድ ግሽበቱን በስድስት ከመቶ የማውረድ ትልም እንዳለው ባለሥልጣኑ አመልክተዋል፡፡

ዘገባውን ያድምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG