ዋሺንግተን ዲ.ሲ. —
ሶማሊያ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ከማዕከላዊቱ ሂራን ክልል ኤል-አሊ ከተማ ለቅቆ መውጣቱ ተገለፀ፡፡
የጦሩን መውጣት ተከትሎ የአል-ሻባብ ተዋጊዎች ከተማዪቱን መቆጣጠራቸው ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ ወታደሮች ይዞታዎቻቸውን ሲለቅቁ እዚያቹ ሂራን ክልል ውስጥ በቁጥጥራቸው ሥር ከነበሩ ከተሞች መካከል ኤል-አሊ ሁለተኛ መሆኗ ነው፡፡
ሰሞኑን ኤል-አሊ አቅራቢያ በምትገኝ ሞቆኮሪን እንዲሁ ለቅቀው መውጣታቸውን የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች ዛሬ ማለዳ ከለቀቋት ኤል-አሊ ለምን እንደወጡ ለጊዜው ዝርዝር ማግኘት ባይቻልም የእንግሊዝ የዜና ወኪል - ቢቢሲ የአል ሻባብን ራዲዮ አንዳሉስን ጠቅሶ ባሠራጨው ዜና ጦሩ ሠፍሮበት የነበረው መደብ መደብደቡን አመልክቷል፡፡
በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ጦር - የአሚሶም አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ኤል አሊ ከተማን ለቅቆ መውጣቱን የከተማዪቱ ከንቲባ አደን አሊ ፊዶው ለቪኦኤ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን ድምፅ ያዳምጡ።