በውጭ ሀገራት፣ ከኢትዮጵያ፥ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሠራተኞች ድረስ የመቅጠር ፍላጎት እንዳለ፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገለጹ፡፡
ዛሬ፣ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተጀመረው የሥራ ፈጠራ መድረክ ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በኢትዮጵያ፣ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ለእነዚኽ ዜጎች፣ በዋናነት የሥራ ዕድል መፍጠር ያለበት፣ የግሉ ዘርፍ እንጂ መንግሥት እንዳልኾነ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ሚና፣ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ኹኔታን መፍጠር እንደኾነ የገለጹት አቶ ንጉሡ፣ በዚኽ ዓመት ከተፈጠረው 3ነጥብ1 ሚሊዮን የሥራ ዕድልም አብዛኛው፣ በግሉ ዘርፍ መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ በአፍሪካ፣ ለሥራ ዕድል መፈጠር፣ የተለያዩ ፈተናዎች እንዳሉ በተገለጸበት በዚኽ መድረክ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት፣ በአህጉሪቱ፣ 200 ሚሊዮን ሥራዎች እንደታጠፉ ተነግሯል፡፡ በአፍሪካ፣ በየዓመቱ 19 ሚሊዮን ዐዲስ ሥራ ፈላጊዎች ቢኖሩም፣ በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር እንዳልተቻለም ተገልጿል፡፡