ኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የሠላም ሥምምነት መፈረሙን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ በመግባት ላይ ይገኛል።
ትናንት በሁለት ዕቃ ጫኝ መኪኖች አስቸኳይ መድሃኒት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የሕክምናና የቀዶ ሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ መቀሌ የላከው ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ዛሬ የሙከራ በረራውን ወደ ሽረ ማድረጉን ገልጿል። ወደ ትግራይ ክልል እንደገና በረራ መጀመሩ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ችግር እንደሚያቃልል ገልጿል።
በሌላ በኩል የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትዊተር ገጹ ላይ ባጋራው መልዕክት እርዳታ የያዙ መኪኖቹ ከሰኔ 2014 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ በጎንደር አቋርጠው ዛሬ ማይ-ጸብሪ ከተማ እንደደረሱና በሚቀጥሉት ቀናት እጅግ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ምግብ በከተማው ላሉ ተረጂዎች እንደሚሰራጭ አስታውቋል።
ተጨማሪ ምግብና የሕክምና ቁሳቁሶች በተገኘው መንገድ ሁሉ መላክ እንደሚቀጥልም ድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ዛሬ የሙከራ በረራ ወደ ሽረ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ በትናንትናው ዕለት በሁለት ዕቃ ጫኝ መኪኖች አስቸኳይ መድሃኒት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የቀዶ ሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ መቀሌ ልኳል።
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ክንደያ ገብረህይወት “ሁለት እርዳታ የጫኑ መኪኖች መቀሌ መድረሳቸውን አየሁ” ሲሉ ትናንት በትዊተራቸው አስታውቀዋል። “በተቁስ ማቆሙ ሥምምነት መሠረት ተጨማሪ እርዳታ በቅርቡ ይመጣል ብዬት ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉም አክለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ግጭት 2.5 ሚሊዮን ሰዎችን ከቤታቸው ሲያፈናቅል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን የምግብ እርዳታ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል።
ካለፈው ነሐሴ ወዲህ ርዳታ ወደ ትግራይ ሲገባ ትናንት የመጀመሪያው ነው።
ጦርነቱ ከሁለት ዓመታት በፊት ከጀመረ በኋላ የሰብዓዊ አቅርቦት ገደብ መኖሩ፣ በትግራይ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ የምግብና የመድሃኒት ዕርዳታ እንዲሹ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የአይሲአርሲ ቃል አቀባይ ጁዴ ፉህኒ “በቀጣዮቹ ቀናት” ተጨማሪ ምግብ እና መሰረታዊ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በአየርና በተሽከርካሪ ተጨማሪ እርዳታ ወደ ትግራይ እንደሚደርስ ተናግረዋል ።
“ዛሬ የገባው እርዳታ ለትግራይ ሕዝብ ተስፋ የሚሰጥ ነው። በተጨማሪም እርዳታው ለበርካታ ህሙማን በህይወት የመቆየት ተስፋን ይሰጣል።” ብለዋል።
አያይዘውም “በመድሃኒት እጦት፣ በሕክምና እርዳታ አለመኖር፣ የጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች መድኃኒት አለመኖር ምክንያት በክልሉ ብዙ ሰዎች ለሞት ይጋለጡ ነበር። አንዳንዶቹ ሆስፒታሎች አገልግሎት አቁመዋል፣ እንዲሁም በክልሉ ያለው የጤና አገልግሎት ሥርዓት በአጠቃላይ ትልቅ ጫና ውስጥ ነበር።” ብለዋል።
ባለፈው ወር በተደረገ ምርመራ በትግራይ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሕጻናትና ሦስት እጅ የሚሆኑት የሚያጠቡ አናቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው ታውቋል።
የቀይ መስቀል ኮሚቴው ወደ ሽረ የሙከራ በረራ ያደረገው ከተማው በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት በመሆኑ ነው። በረራ መቀጠሉ ”አስቸኳይ እርዳታ የሚሹ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ችግር ያቃልላል” ብሏል ኮሚቴው።
በዓለም ምግብ ፕሮግራም በጎንደር በኩል የተላከው እርዳታ፣ በህወሓት የሚመሩት ኃይሎች ጥቃት መጠናከርን ተከትሎ፣ የፌዴራል መንግሥቱና አጋር ኃይሎች በሰኔ 2014 ከትግራይ ጦራቸውን ካወጡ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ መሪዎች፣ ባለፈው ጥቅምት 23 ቀን በፕሪቶሪያ የተፈረመው የተኩስ አቁም ሥምምነት ተግባራዊ የሚደረግበትን የትግበራ አፈጻጸም በተመለከተ በኬንያ ሥምምነት ላይ ደርሰዋል።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥት ወገን ዋና ተደራዳሪ የሆኑትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትግራይ አገልግሎቶች “እንዲቀጥሉ እየተደረገ ነው” ሲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው ትናንት በፓርላማ እንዳሉት መንግሥታቸው የሠላም ሥምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኛ ነው።
በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሠላም ሥምምነት ሁለቱም ወገኖች ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲገባ እንዲያመቻቹ፣ እንዲሁም የስልክ፣ ኢንተርኔትና የባንክ አገልግሎት እንዲቀጥል እንዲያደርግ የሚጠይቅ ነው። አገልግሎቶቹ እስከአሁን አለመቀጠላቸው ታውቋል።
ሥምምነቱ በተጨማሪም ለሰብዓዊ ሠራተኞች የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ ይጠይቃል።
/ፍረድ ሃርተር ከአዲስ አበባ ያጠናቀረው ዘገባ ነው። ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎች ተካተውበታል/