በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ በቅርቡ ካወጣችው ፀረ-ሽብር ሕግ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ክሦች እየታዩ ነው


ባለፈው ዓመት ተይዘው በዚሁ ሕግ የተከሰሱ 150 ሰዎችን ጉዳዮች ሦስት ዳኞች የተሰየሙበት ፌደራል ችሎት እየተመለከተ ነው፡፡ ከተከሣሾቹ መካከል ታዋቂ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ይገኙባቸዋል፡፡

ላለፉት ጥቂት ወራት በአዲስ አበባው ልደታ ፌደራል ፍርድ ቤት የሚካሄደውን የሽብር ክሦች ሂደት ለመታዘብ አንድ አነስተኛ የዲፕሎማቶችና የጋዜጠኞች ቡድን በየሣምንቱ ወደዚያ ይሄዳል፡፡

በቅርቡ የፔን አሜሪካ “የመፃፍ ነፃነት” ተሸላሚ የሆነው የእስክንድር ነጋና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃውሞ ውስጥ እየተነሣ ያለ ኮከብ ነው የሚባለው አንዱዓለም አራጌ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረትን የሣቡ ናቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች የሽብር ጥቃቶችን ያካሂዳል በሚል በመንግሥቱ ከታገደው ግንቦት ሰባት ጋር ተባብራችኋል ተብለው ነው የተከሰሱት፡፡

ባለፈው ሣምንት ብይን ሊሰጥ ቀጠሮ በተያዘ ጊዜ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሣደር ዶናልድ ቡዝ (Booth) በችሎቱ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዳኞቹ ተጨማሪ ጊዜ እንፈልጋለን ሲሉ ብይኑን ለሰኔ ቀጥረዋል፡፡

ኦጋዴን ውስጥ በሕግ ከታገደው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር አባላት ጋር ሲንቀሣቀሱ ተይዘው የተከሰሱት የስዊድን ጋዜጠኞች ጉዳይ ከሌሎቹ ለችሎቱ ከቀረቡ ዶሴዎች መካከል ይገኛል፡፡ ጋዜጠኞቹ የተከሰሱት ሽብር ፈጠራን ትደግፋላችሁ ተብለው ሲሆን የ11 ዓመት እሥራት ፍርድ እንደተላለፈባቸው ይታወሣል፡፡

የአንድ ሕትመት ያቋረጠ ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅና የአንድ ሌላ ጋዜጣ ቋሚ ፀሐፊም እንዲሁ በሽብር ፈጠራ ተከስሰው የረጅም ጊዜ እሥራት ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡

ሌላው በክሥ ላይ ያለ ጉዳይ ደግሞ ባለፈው ዓመት ኦጋዴን ውስጥ የተጠለፉ ሁለት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሠራተኞችን ለማስለቀቅ በተደረገ ድርድር ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የፀጥታ መኮንን ጉዳይ ነው፡፡ ታጋቾቹ እንደተለቀቁ እኒህ የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኛ ከኦብነግ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

አንድ መቶ የሚሆኑ የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎች የሆኑ እሥረኞች ጉዳይ ከሰዉ ዕይታ ሊረሣ ጥቂት የቀረው ጉዳይ ይመስላል፡፡ አቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክሥ በሕገወጥነት ከተፈረጀው ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጋር ተባብራችኋል የሚል ሲሆን ከተከሣሾቹ መካከል የሁሉቱ ትላልቅ ናቸው የሚባሉት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችና የቀድሞ የፓርላማ አባል ይገኙባቸዋል፡፡

የእነዚህ ጉዳዮች እንዲህ መብዛት በኢትዮጵያው ፀረ-ሽብር ሕግ ላይ ዓለምአቀፍ ትኩረትና ዐይን እንዲበዛ አስገድዷል፡፡ ሕጉ ባለፈው ዓመት ግንቦት ሰባት፣ ኦብነግ፣ ኦነግና አልቃይዳ የሽብር ቡድኖች ናቸው ተብሎ እንደታወጀ ሥራ ጀምሯል፡፡

“ተቃውሞን መበተን” በሚል ርዕስ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥታ ሕግጋትንና ሽብር ፈጠራን መዋጋት የሚለውን ሰበብ የውስጥ ትችቶችንና ተቃውሞን ለማፈን እየተጠቀመበት ነው ሲል ከስሷል፡፡

ዝርዝሩን ከመለስካቸው አምኃና ከፒተር ሃይንላይን ዘገባዎች አዳምጡ

XS
SM
MD
LG