በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መንግሥት ያቀረበው  የ582 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጥያቄ በፓርላማ ጸደቀ


 Addis Ababa, Ethiopia
Addis Ababa, Ethiopia

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን የ582 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የበጀት ጥያቄ አጸድቋል፡፡ ይህም በአጠቃላይ የፌዴራል መንግሥቱን የ2017 ዓ.ም. በጀት ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ አድርሶታል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ፣ ተጨማሪ በጀት አቅርበው ባጸደቁበት ወቅት በጀቱ አስፈልጓል ያሉበትን ምክኒያት አብራርተዋል።

ከ582 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ውስጥ 185 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ፣ 208 ቢሊዮን ብር ለማኅበራዊ ድጎማ፣ 60 ቢሊዮን ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት ማስፋፊያ፣ 10 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ፕሮጄክቶች ማስተካከያ እና የተቀረው 119 ቢሊዮን ብር ለወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ የሚውል እንደሆነ አቶ ተስፋዬ ዘርዝረው ተናግረዋል።

ለተጨማሪ በጀቱ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 281ነጥብ 5 ቢሊዮን ብሩ ከታክስ (ግብር) የሚገኝ እንደሆነ እና የተቀረው ደግሞ ከውጭ ሀገራትበሚገኝ ርዳታ እና ብድር የሚሸፈን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ተከትሎ ከምክር ቤት አባላት፣ የበጀቱን መጠን፣ በዋጋ ንረት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የተያዘውን በጀት የተመለከቱ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የተባሉ አባል፣ “ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ካጸደቅን በኋላ የዛን ከግማሽ በላይ መጨመር ከኢኮኖሚ ቀመር አንጻር አልተጋነነም ወይ? ይህ እንዴት ማሻሻያ ሊባል ይችላል” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ በሰጡት ምላሽ፣ ተጨማሪ በጀቱ እንዲያውም ከሀገሪቱ አቅም አንጻር የሚያንስ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡ “የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር ነው፡፡ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርታችን (ጂዲፒ) 200 ቢሊዮን አካባቢ ደርሷል፡፡ ከዚህ አንጻር በጀታችን ገና ነው፤ ከዚህም በላይ ማደግ አለበት” ብለዋል፡፡ “እንዲያውም ገቢያችን እየተሸሻለ ሲመጣ የሚቀጥለው ዓመት ላይ የምናቀርበው በጀት ከዚህ እጅግ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል” ሲሉም አክለዋል፡፡

ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ንረትን ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን የገለጹ የምክር ቤት አባላትም አሉ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፣ የበጀቱን ምንጭና ከዚህም ለወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ የተያዘውን መጠን በማንሳት፣ ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ንረትን የሚቀንስ እንጂ የሚያባብስ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በብድር እና በርዳታ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ድጋፍ መገኘቱን፣ የተቀረውም በግብር የሚሸፈን መኾኑ፣ እንዲሁም ከተጨማሪ በጀቱ 119 ቢሊዮኑ ከብሔራዊ ባንክ ብድር ሊሸፈን የነበረው የበጀት ጉድለት የሚሸፈንበት መሆኑ፣ የዋጋ ንረትን የሚከላከሉ እንደሆኑ አስረድተዋል።

መንግሥት አስቀድሞ ይዞ ከነበረው 971ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ፣ የ358 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት መኖሩ ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

ተጨማሪ በጀቱ በዋጋ ንረት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽዕኖ ይኖር እንደሆን ባለፈው ሳምንት ዓርብ አስተያየታቸውን የሰጡን የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሞያው ዶ/ር ቴዎድሮስ መኮንን፣ የዋጋ ንረት የሚፈጠረው ገንዘብ በህትመት መልክ ወደ ኢኮኖሚው ሲቀላቀል እንደሆነ በመግለጽ የበጀት ጭማሪው ምንጭ ከዚህ ውጭ በመሆኑ በዋጋ ንረት ላይ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ አይኖረውም ሲሉ አብራርተው ነበር፡፡

በዛሬው የምክር ቤት ውሎ፣ "ለካፒታል ፕሮጄክቶች የተያዘው የበጀት መጠን አንሷል" በሚልም ከዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ እና ከወ/ሮ ቅድስት አርአያ ጥያቄዎች ተነስተው በሚኒስትሩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

አዲስ የሚጀመሩ የካፒታል ፕሮጄክቶች አለመኖራቸውን የተናገሩት አቶ አሕመድ፣ “ለነባር የካፒታል ፕሮጄክቶችን እንደየ ባሕሪያቸው ፋይናንስ ማድረጋችንን እንቀጥላለን። በምንዛሬ ለውጡ ምክንያት ለሚኖር የወጪ ጭማሪ 10 ቢሊዮን ብር የማስተካከያ በጀት ይዘናል” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም፣ የአብኑ ተመራጭ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ ከውጭ ምንዛሬ ለውጡ አንጻር የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ አነስተኛ እንደሆነ ጠቅሰው ምንዛሬውን የሚመጥን ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ የደሞዝ ጭማሪው ከመንግሥት አቅም አንጻር “በተለይ ለዝቅተኛ ተከፋዮች በጣም ከፍተኛ ጭማሪ ነው የተደረገው” ያሉ ሲሆን፣ ሆኖም በቂ እንዳልሆነ እና ከአገሪቱ አቅም ጋራ እየተስተካከለ እንሚሄድ ገልጸዋል፡፡

ለማኅበራዊ ድጎማዎች የተያዘው በጀት ከፍ ያለው፣ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ የሚኖረውን ጫና ለመቀነስ በመታሰቡ እንደሆነ፣ የዕዳ ክፍያ ከፍ ያለው ደግሞ በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት ለብድር የሚመለሰው በብር መጠኑ በመጨመሩ እንዲሁም የልማት ድርጅቶችን የንግድ ባንክ ዕዳ ለማቃለል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከተጨማሪ በጀቱ ውስጥ ከ281 ቢሊዮን ብር በላይ በግብር ገቢ እንደሚሸፈን የተገለፀ ሲሆን፣ ይህ በግብር ከፋዩ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል እና እየተቀዛቀዘ ነው ያሉትን የንግዱን ዘርፍ ይበልጥ ሊጎዳው ይችላል በሚል የጠየቁም አሉ፡፡ አቶ አሕመድ ሺዴ በሰጡት ምላሽ፣ በኢትዮጵያ ያለው የግብር አሰባሰብ ሂደት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት እና ከሌሎች አገራት አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ከመጥቀስ ባለፈ በንግድ ሥርዓቱ ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ አላብራሩም፡፡

ውይይቱን ተከትሎ፣ ለ2017 ዓ፡ም የቀረበው የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ በጀት በሦስት ተቃውሞ እና በአምስት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል፡፡ ይህም፣ ከዚህ ቀደም የጸደቀውን 971፡2 ቢሊዮን ብር ጨምሮ የፌዴራል መንግስቱን የ2017 አጠቃላይ በጀት ከ1፡5 ትሪሊዮን ብር በላይ እንዲሆን አድርጓል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG