በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኬንያ እና በዩጋንዳ ለታቀደው ከሶማሊያ ጋራ የማሸማገል ርምጃ ኢትዮጵያ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠች


በኬንያ እና በዩጋንዳ ለታቀደው ከሶማሊያ ጋራ የማሸማገል ርምጃ ኢትዮጵያ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:32 0:00

በኬንያ እና በዩጋንዳ ለታቀደው ከሶማሊያ ጋራ የማሸማገል ርምጃ ኢትዮጵያ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠች

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፣ ዛሬ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኬንያን እና የዩጋንዳን የሽምግልና እቅድ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ተጠይቀው በሰጡኢት ከሶማሊያ ጋራ ለሚደረግ ድርድር ኢትዮጵያ ዝግጁ መኾኗን አስታውቀዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ “የቀጣናውን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል” ያሉትን በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ከዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ ቅዳሜ ዕለት ተናግረዋል።

ለዚህ የጥረት ዕቅድ የኢትዮጵያ ምላሽ ምን እንደኾነ የተጠየቁት አምባሳደር ነቢያት፣ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት ለሚደረጉ ድርድሮች ዝግጁ እንደኾነች ገልፀዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ከመጀመሪያውም ጀምሮ ማናቸውም ዐይነት ልዩነቶች በውይይት እና በሰላም ድርድር እንደሚፈቱ ፅኑ እምነቷ ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ “ለዚህም ነው በተለያዩ መድረኮች ላይ ቀርባ አቋሟን በማስረዳት፣ ዘላቂ ለሆነ፣ ሁለቱንም ሀገራት ሊያስማማ ወደሚችል አቅጣጫ ለመሄድ አጋዥ ሚና ስትጫወት የቆየችው” ሲሉ አክለዋል፡፡

“ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሰላም መድረኮች የሸሸችበት አጋጣሚ የለም” በማለትም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም “የተለያዩ የሰላም ሂደቶች ተነስተዋል፣ የአንካራው ተነስቷል፣ አሁንም ፖቴንሺያሊ ሊነሱ የሚችሉ አሉ” ብለዋል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት በኬንያ እና ኡጋንዳ የሽምግልና ጉዳይ ላይ ስላለው አቋም በይፋ የገለፀው ነገር የለም፡፡

የኬንያው ፕሬዝደንት፣ ከኡጋንዳው አቻቸው ጋራ ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ለማሸማገል እንደሚጥሩ የተናገሩት፣ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ 24ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤውን ባካሄደበት ታንዛኒያ፣ አሩሻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፣ ፕሬዝደንት መሀሙድ፣ ሩቶ እና ሙሴቬኒ በጉባዔው ላይ ተገናኝተው መነጋገራቸውን ቢገልፅም ከኢትዮጵያ ጋራ ስላለው ውጥረት ሽምግልና ሊኖር እንደሚችል ግን አልጠቀሰም። የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም ፊቂ፣ ከዚህ ቀደም ለተደረጉ ሽምግልናዎች አለመሳካት ኢትዮጵያን ተጠያቂ ማድረጋቸውን የገለፀው ሮይተርስ፣ ስለቀጣይ የሽምግልና ጥረቶች ያሉት ነገር ስለመኖሩ ግን በዘገባው አላካተተም፡፡

ኢትዮጵያ፣ ራሷን ነጻ አገር አድርጋ ከምትቆጥረው ከተገንጣይዋ ሶማሊላንድ ጋራ በተፈራረመችው አወዛጋቢ የባሕር በር የመግባቢያ ሰምምነት ምክንያት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤት አላስገኙም፡፡

ቱርክ ፣ ችግሩን ለመፍታት በሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ሁለት ስብሰባዎችን በአንካራ ላይ አመቻችታ የነበረ ሲኾን፣ የሁለቱ አገራት ልዑካን ፊት ለፊት ሳይገናኙ በተናጥል ባደረጉት ውይይት መግባባት አልቻሉም፡፡

የሶማሊያ ባለሥልጣናት፣ የመግባቢያ ሰነዱ እስካልተሰረዘ ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም አይነት ቀጥተኛ ንግግር እንደማይኖር አጽንኦት ሲሰጡ ሰንብተዋል።

ከዚህም ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ እንደማትሳተፍ ሶማሊያ አቋም ይዛለች፡፡

ይህን ተከትሎ፣ ነባሩ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ስምሪት ሲያበቃ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ለቆ ሊወጣ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

በዛሬው መግለጫ ላይ ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው፣ ስለጦሩ መውጣት አስተያየት ባይሰጡም የፀረ አልሻባብ ውጊያው ግን እንደሚቀጥል በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

ቃል አቀባዩ “ከሶማሌ አካባቢ …በርካታ ተንኳሽ እና ኃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮች ቢሰሙም፣ ኢትዮጵያ በኃላፊነት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ከመስራት ወደኋላ ሳትል እሱኑ ተከትላ እየሰራች ነው የምትገኘው” ብለዋል፡፡ “በቀጣይም ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚኖራት ተሳትፎ ለቀጣናው ብቻ ሳይሆን፣ ከቀጣናውም ተሸጋሪ የሆኑ የሰላምና አለመረጋጋት ምንጮችን ማድረቅ የሚቻልበት ሂደት ላይ ከሌሎች አጋሮች ጋር ሆና ቁልፍ ሚና መጫወቷን ትቀጥላለች” ሲሉም አክለዋል፡፡

ምክንያቱም “በአካባባው አሸባሪው አልሻባብ ኬሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት፣ በሚገኘው ክፍተት ሁሉ ከቀጣናው ባለፈ ለዓለም ስጋት እንደሚሆን ስለሚታወቅ ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት በዛሬው መግለጫቸው በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ “በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታለው ወደ ሚያንማር የገቡ እና ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያውያንን ለማስለቀቅ፣ ጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሚያንማር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ጋራ የኦንላይን ስብሰባዎች አካሂዷል” ብለዋል፡፡

መሰል ችግር ያጋጠማቸው የሌሎች 18 አገራት ኤምባሲዎችም በውይይቱ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በሊባኖስ ለደኅንነታቸው አስጊ በሆነ ኹኔታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረትም እንደቀጠለ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ 2 ሺህ ዜጎች እንደሚመለሱ፣ ከነዚህም ውስጥ 200ው ከሳምንት በኋላ ወደ አገራቸው እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG