በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሸቀጥ እጥረት


የኢትዮጵያ መንግሥት ስኳርና ዘይት እያቀረበ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በ18 መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጣሪያ ከጣለ ወዲህ ከጥር ወር ጀምሮ ስኳር፣ ዘይትና ሌሎችም አቅርቦቶች ከመደበኛዎቹ ኪዎስኮች መደርደሪያዎች ላይ ርቀዋል፡፡

መንግሥት የደነገገው የሸቀጥ ዋጋ ጣሪያና ቁጥጥር ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ የተፈጠረውን ከፍተኛ የገበያ እጥረት ለመሸፈን መሠረታዊ የምግብ አቅርቦቶችን እራሱ በቀጥታ ለሸማች ማቅረብ ጀምሯል፡፡

'በአዲስ አበባ የመንግሥት ሱቆች ደጅ ዘይትና ስኳር ፍለጋ የሚኮለኮሉት ረጃጅም የወረፋ ሰልፎች የተለመዱ ትዕይንቶች ሆነዋል' ይላል ዘጋቢያችን ፒተር ሃይንላይን፡፡

የሸቀጦች ዋጋ ጣሪያ የወጣው በቱኒዝያ የተከሰተው የምግብ ዋጋ መናር የጫረው ቁጣ በሰሜን አፍሪካና በመላው መካከለኛው ምሥራቅ ከባድ ሕዝባዊ አመፅና የዐረቡን ዓለም አብዮት ባቀጣጠለበት ሰሞን ነበር፡፡

በገበያው ውስጥ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት 'በገንዘብ እጥረት እየተሰቃየ ላለው፣ ባሻቀበው የዓለም የምግብ ዋጋ ምክንያት ለሚንገላታው ሕዝብ ፈጣን መድኅን ሊሰጥ ይችላል' በሚል የሃገሩ መገናኛ ብዙኃን በአድናቆት አሞካሽተውት እንደነበር ፒተር በዘገባው ጠቁሟል፡፡

ባለሱቆቹ ግን አኮረፉ፡፡ የተጣለባቸው ጣሪያ በቂ የሆነ ትርፍ እንደማያስገኝላቸው በመግለፅ በኪሣራ ለመነገድ ከቶውንም እንደማይሞክሩ ተናገሩ፡፡

እነዚያ ተመን የወጣባቸው ሸቀጦች ከገበያው ሲጠፉ መንግሥት በተራው አቅራቢዎች 'ሰው ሠራሽ እጥረት ፈጥረዋል' ሲል ከሠሠ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ይህንኑ የመንግሥታቸውን ክሥ አስተጋብተዋል፡፡

ነጋዴዎቹ በተደነገገላቸው ዋጋ ለማቅረብ እስኪስማሙና ወደ ንግዱ እስኪመለሱ መንግሥት እነርሱን ተራምዶ እራሱ ለሸማቹ ሸቀጥ እንደሚያቀርብ አስታወቁ፡፡

"ገበያው ለውድቀት የተዳረገው ጅምላ አቅራቢዎችና ቸርቻሪዎች የተጋነነ ትርፍ ለማጋበስ በመፈለጋቸው መሆኑን ያደረግነው ጥናት ያሣያል" የሚለው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነጋዴዎቹ ከዘይትና ከስኳር የሚያገኙት ትርፍ ከ4 እስከ 6 ከመቶ እንዳይበልጥ መቁረጡን አመልክቷል፡፡

የዋጋ ጣሪያው፣ ቁጥጥሩና የመንግሥቶቹ ሱቆች ገበያው እስኪረጋጋ ብቻ የሚቆዩ ጊዜያዊ መፍትሔ መሆናቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢጠቁምም የገበያ ሊቃውንትና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ግን እንዲህ ዓይነቱ በሸማችና ሻጭ መካከል ያለ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እየተናገሩ ይተቹታል፡፡

"ይህ የዋጋ ጣሪያ መንግሥት ከሚያራምደው ምጣኔኃብቱን በገዘፈ አብላጫ የመቆጣጠር የቆየ አባዜ አንድ ተጨማሪ እርምጃ ነው" የሚሉት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ እየጨመረ ባለው መንግሥት ፖሊሲዎቹ በከሸፉበት ቁጥር የግሉን ዘርፍ ጭራቃዊ ገፅታ የማላበስ አካሄድ ውስጥ ከባድ አደጋ እንደሚታያው አመልክተዋል፡፡

እነዚያ ዛሬ ዘይትና ስኳር ከመንግሥቶቹ የሕብረት ሱቆች ለመግዛት የተሰለፉ ሸማቾች በመሃላቸው የሚያጉተሞትሙት ብዙ ነገር እንዳለ ፒተር በዘገባው ማብቂያ ጠቆም ያደርጋል፤ "ምግብ በራሽን ወደሚታደልበት ወደዚያ ወደራቀው ዘመን እንደመለስ ይሆን እንዴ?" ሰዉ ሥጋቱን ይናገራል፡፡

ተጨማሪ ዝርዝር ከዘገባው ያዳምጡ፡፡

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG