በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ስለ ጣልቃገብ ጫናዎች” ተናገሩ


ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ስለ ጣልቃገብ ጫናዎች” ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:52 0:00

በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ፕሪቶሪያ - ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ድርድሩ የቀጠለ ሲሆን 'ከግራና ከቀኝ ከባድ የውጭ ጣልቃ ገብነት አለ' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለቻይና የመንግሥት ቴሌቪዥን (ሲጂቲኤን) ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የውጭ ጣልቃገብነት” ሲሉ ማንን ማለታቸው እንደሆነ በዝርዝር ባይናገሩም “ከርቀት ከመስማት ይልቅ የራሳችንን ህግ፣ ባህልና ወግ አክብረን ከሠራን ሰላም ይጨበጣል” ብለዋል።

አክለውም “ህወሓት የሃገሪቱን ህግ፣ “የራሳቸው” ያሉትን ህገመንግሥት እንዲያከብር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ አንድ ክልል [ስቴት] እንዲንቀሳቀሱ ለማሳመን እየሞከርን ነው፤ ይህ ከሆነ ሠላም ላይ ይደረሳል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሲጂቲቪ በሰጡት ቃል ያነሷቸው እነዚህ ነጥቦች በፕሪቶሪያው መድረክ ላይ እንደቅድመ ሁኔታ ተቀምጠው ይሁን ወይም የመነጋገሪያ አጀንዳ ውስጥ ይካተቱ አይካተቱ ከዚያ የወጣ ምንም መረጃ ባለመኖሩ ማወቅ አልተቻለም።

የመንግሥቱ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች እርዳታ እየደረሰና አገልግሎቶችን ለማስጀመር እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በቴሌቪዥን ጣቢያው የፌስቡክ ገፅ ላይ ትናንት፣ ሰኞ ጥቅምት 21 ከመውጣቱ በስተቀር የት ሆነውና መቼ እንደተናገሩ የተያያዘ መረጃ የለም።

ከህወሓትም ይሁን ከሌላ አካል ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቃል የተሰማ ምላሽ እስካሁን የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሠላም ንግግሩ ወደ ሌላ ሣምንት መራዘሙ “ፓርቲዎቹ ወደ ንግግሩ ሲመጡ በመካከላቸው ‘ትንሽ የተራራቀ ሃሳብ’ ይዘው ስለመምጣታቸው አመላካች ነው” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

“ፓርቲዎቹ በሚለያዩበት ዙሪያም በመነጋገር በመካከላቸው ያለውንም ርቀት ማጥበብ ያስችላል ብለን በምንመኘው መሠረት ፈቃደኛ ሆነው አብረው መቀመጥ መቀጠላቸው በራሱ ገንቢ ድባብ ለመፈጠሩ አመላካች ነው” ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ “መጠነ ሰፊ የጭካኔ አድራጎቶች ሊፈፀሙ ይችላሉ” የሚል ሥጋት እንዳላትም ቃል አቀባዩ በድጋሚ ገልፀዋል።

በሌላ ዜና በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ልዑክ “የወጣ ነው” የተባለና “የኤርትራና የኢትዮጵያ ኃይሎች ትግራይ ውስጥ ጥቃታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን የሚናገርና የሚያወግዝ፣ እንዲሁም የህወሓት ተዋጊዎች እየወሰዱ ነው ያለውን ‘የመከላከል አድራጎት’ የሚያደንቅ ፅሁፍ እየተጋራ የተሽከረከረ ሲሆን የኅብረቱ ልዑክ ቢሮ ግን መልዕክቱን አስተባብሏል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ ፅህፈት ቤት ሳይቱ ላይ የኢንተርኔት ሰርጎገብ ጥቃት መፈፀሙን ወዲያው ባወጣው መግለጫ ጠቁሞ “የተሠራጨው ፅሁፍ የአውሮፓ ኅብረት ወይም የልዑኩ ይፋ መግለጫ አይደለም፤ ጥቃት የተፈፀመበትን ሳይት መልሰን ተቆጣጥረናል፣ ሰርጎገብ ጥቃቱንም እየመረመርን ነው” ብሏል።

XS
SM
MD
LG