ከኢትዮጵያ በስተደቡብ በሚገኙ ልዩ ልዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ ከሰባት ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ፡፡ እነዚህን የታሰሩ ዜጎችን ለማስመለስ ጥረት መጀመሩንም ጨምሮ ገልጿል።
ታሳሪ ኢትዮጵያውያኑ፣ መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ለማድረግ በሕገ ወጥ መንገድ ሲጓዙ በተለያዩ ሀገራት የተያዙ እንደኾኑ የገለጹት፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር. ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ መንግሥት፥ እስረኞቹን ለማስመለስ ጥረት መጀመሩን፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኦኤም)፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲያካሒድ የቆየውን የኢትዮጵያ መርሐ ግብር መጠናቀቁን አስመልክቶ፣ በዛሬው ዕለት በተዘጋጀ ሥነ ሥርዐት ላይ አስታውቀዋል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ፣ በእስር እና በተለያዩ ችግሮች ላይ የነበሩ ከ130 ሺሕ በላይ ዜጎች መመለሳቸውን ያወሱት ሚኒስትሯ፣ በደቡብ እና ምሥራቅ አፍሪካ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን የመመለሱ ሥራም፣ ከሳዑዲ አረቢያው ሒደት በተገኘ ልምድ ላይ ተመሥርቶ እንደሚካሔድ አብራርተዋል፡፡ ይኸው ተሞክሮ፣ ኢትዮጵያውያንን በሕጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ መላክንም እንደሚያካትትና ሥራውም መጀመሩን ዶር. ኤርጎጌ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በበኩሉ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ በመተባበር፣ 11ሺሕ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን ከልዩ ልዩ ሀገራት፣ ደኅንነታቸው በተጠበቀ መንገድ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ መልሶ የማቋቋም ሥራ ማከናወኑን ገልጿል፡፡
መደበኛ ባልኾነ መንገድ ከሀገራቸው ወጥተው ለችግር የሚዳረጉ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን የመመለሱን ተግባር፣ ከአጋር አካላት ጋራ ማከናወኑን እንደሚቀጥልም፣ የአይኦኤም ኢትዮጵያ ሓላፊ አቢባቱ ዋኔ፣ በዛሬው የማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ ተናግረዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡