በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግስት የአንዳርጋቸዉ ጽጌ አያያዝ የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት አደጋ ላይ እንዳይጥል እንግሊዝ አሳሰበች


አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ /ፎቶ ከኢንተርኔት የተገኘ/
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ /ፎቶ ከኢንተርኔት የተገኘ/

ቀጥተኛ መገናኛ

የተቃውሞ መሪውና ዜጋውም የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘበት ሁኔታ “ጨርሶ ተቀባይነት የሌለውና በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያለውን ግንኙነትም የሚጎዳና አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ሲል የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን ትናንት አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የእንግሊዝን መንግሥት ስሞታ ያስተባብላል፡፡

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ ትናንት በሰጡት መግለጫ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ አቻቸው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር መወያየታቸውንና “ብርቱ” ያሉትን መልዕክት ያስተላለፉላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእንግሊዙ የዜና አውታር ሮይተርስ እንደዘገበው ሚስተር ሃሞንድ ከዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት መግለጫ “እንግሊዛዊው ዜጋ አንዳርጋቸው ፅጌ ከታሠሩ አንድ ዓመት ቢያልፍም የመታሠራቸውን ጉዳይ በሕግ ፊት ለመሟገት እንኳ ሳይቻል ብቻቸውን ተነጥለው እንዲቆዩ ተደርጓል” ብለዋል፡፡

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አክለውም የአቶ አንዳርጋቸው ደኅንነት በእጅጉ እያሳሰባቸው መሆኑንና የእንግሊዝ ቆንስላ አቶ አንዳርጋቸውን በየወቅቱ ማግኘት እንዲችል ለማድረግ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቃል ቢገባም በተደጋጋሚ የቀረቡት ጥያቄዎች ግን ያለመልስ መምከናቸው ያሳዘናቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የእንግሊዝ መንግሥት ባለፈው ነኀሴ ሎንዶን የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጉዳይ ፈፃሚ መልዕክተኛ ጠርቶ አቶ አንዳርጋቸው ላይ ቀደም ሲል ተላልፎ የነበረው የሞት ፍርድ ተፈፃሚ እንደማይደረግ ማረጋገጫ እንዲሰጠው ጠይቆ እንደነበር፡፡

ጉዳዩ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል ያለውን ግንኙት ወደአደጋ እየወሰደው እንደሆነ ማስጠንቀቃቸውን ሮይተርስ አክሎ ዘግቧል፡፡

“ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ያቀረብንላትን ጥያቄ ሳትቀበል መቅረቷ ተቀባይነት የለውም፡፡ የጉዳዩ አለመንቀሳቀስ እንግሊዝ በብዙ የምታከብረውን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለት ወገናዊ ግንኙነት ይጎዳዋል፡፡” ብለዋል ፊሊፕ ሃሞንድ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው የተያዙት በጥሩ ሁኔታ ነው ስትል ኢትዮጵያ የለንደንን ስሞታ ዛሬ አስተባብላለች፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ለሮይተርስ ሲናገሩ ባለሥልጣኖቻቸው ከእንግሊዝ ጋር ሲተባበሩ መቆየታቸውንና አቶ አንዳርጋቸው የሚገኙበትንም ሁኔታ እንደሚያውቁ ገልፀዋል፡፡

“አንዳንዶች ሊስሉ የሚሞክሯቸው አሳዛኝ ታሪኮች መሠረተ ቢስ ናቸው” - ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡ አክለውም ይህ ሁኔታ በግንኙነቶቻችን መንገድ ላይ እንዲቆም ጨርሶ አንፈቅድም ብለዋል፡፡

“ይሁን እንጂ - አሉ አቶ ጌታቸው - እንግሊዛዊያኑ ወዳጀቻችን የሚጠይቁን አንድን የተፈረደበት ሽብርተኛ ያለቅድመሁኔታ እንድንለቅቅ ከሆነ ይህ የማይሆን ነገር ነው፡፡ ይህንን ይረዳሉ ብለን እናምናለን፡፡”

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞን ለማፈን ጋዜጠኞችን፣ የመብቶች ተሟጋቾችን እና ብሎገሮችን እንደሚያስር እየገለፁ በየወቅቱ ቢከስሱም መንግሥቱ ግን በየወቅቱ ሲያስተባብል ይሰማል፡፡

XS
SM
MD
LG