በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር አና የኢትዮጵያ መንግሥት ይወነጃጀላሉ


ሸማቂው ቡድን “መንግሥት ለሣምንት ያህል ባካሄደው ግድያ ቢያንስ አንድ መቶ የሚሆኑ ዜጎች ፈጅቷል” ብሏል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ONLF) “የኢትዮጵያ ኃይሎች በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክልል ውስጥ ያካሂዳሉ” ያለውን የግድያ ዘመቻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲመረምር ጠይቋል።

ሸማቂዎቹ ባወጡት መግለጫ “ድርቅ ባጠቃው የኦጋዴን ክልል ባለፈው ዓርብ የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞች አንዱን ገድለው ሁለት ሌሎች ያፈኑት የሚያካሄዱትን የሲቪሎች ጅምላ ፍጅት ስላዩ ነው” ብለዋል።

ሸማቂ ቡድኑ መንግሥት “ለሣምንት ያህል ባካሄደው ግድያ ቢያንስ አንድ መቶ የሚሆኑ ዜጎች ፈጅቷል” ብሎአል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አብዱራህማን መሃዲ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በስልክ በስጡት ቃለምልልስ ስዎቹ በጅጅጋና ደገሃቡር መካከል በፋፋን ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ገበሬዎችና አርብቶ አደር ሲቪሎች ናቸው። ግድያው ካለፈው ግንቦት ሁለት የጀመረ እስከ ትላንት ግንቦት 8 የተካሄደ መሆኑን ቃልአቀባዩ ተናግረዋል፡፡ “የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2007 ዓ.ም. ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር ጋር ጦርነት የተካሄደበትን የኦቦሌ አካባቢ ለነዳጅ ኩባንያ ለመሸጥ ከህዝብ እያፀዳ ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል በስልክ ለዘጋቢአችን ፒተር ሃይንላይን በሰጡት ቃል “ክሡ መሠረተ ቢስና ሀሰት ነው፣ ሸማቂው ቡድን ተስፋ ከመቁረጥ የሚያወራው ነው” ብለዋል። “ባለፈው ዓርብ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ሠራተኞች ላይ በተጣለ ጥቃት የሚጠረጠሩ በርካታ የሸማቂው ቡድን አባላት በፖሊሶች ቁጥጥር ሥር ውለዋል” ብለዋል።

ያልተገኙት ሁለት የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞች በኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር ታግተዋል የሚል እምነት እንዳለና ይህን ሽብር የፈጸመው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር ነው ብለው ፖሊሶች እንደሚያምኑ አቶ ሽመልስ አመልክተዋል። “ሁለቱን ሠራተኞች አግተው እንደወሰዱ መረጃ አለን” ብለዋል የመንግሥቱ ቃል አቀባይ።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አብዱራህማን መሃዲ ክሡን በማስተባበል፣ ይልቁንስ “የኢትዮጵያ መንግሥት ሲቪሎችን ሲገድል የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞች ስለደረሱበት እነርሱንም በመግደል መረጃ የማጥፋት እርምጃ ነው የወሰደው፤ ተዋሚዎችን እንደ አሸባሪ መግለፁ ግን የተለመድ ነው” ብለዋል።

“ሽብር የሚፈፅመው እራሱ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ መንግሥት ሌሎችን በአሸባሪነት ይከስሣል። የሚናገሩት እውነት ከሆነ ነፃ የሆነ መርማሪ አካል ወደ አካባቢው ሄዶ ጉዳዩን እንዲያጣራ ይፍቀዱ። በኛ በኩል ማንኛውም ነፃ የሆነ አካል ወደ አካባቢው ገብቶ ማን ሕዝብ ላይ በደል እየፈጸመ እንደሆነ እንዲያጣራ ሁልጊዜም እንደጠየቅን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ፍልሚያ የሚያካሄድበት ክልል ገለልተኛ አካል እንዳይገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ስለሚያግድ ሁለቱ ወገኖች የሚያቀርቡትን ክስ ማጣራት አይቻልም።

በኦጋዴን ክልል እየተባባሰ በሄደውድርቅ ምክንያት ወደ አንድ ሚሊዮን ነጥብ ሦስት ሰው (ከህዝቡ አንድ አራተኛ በላይ ማለት ነው) አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው እየተነገረ ነው፡፡

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG