በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄውን አሁንም እያቀረበ ነው፡፡


በአወሊያ መስጊድ የተሰበሰቡ ሙስሊም አማንያን /ፎቶ - ፋይል/
በአወሊያ መስጊድ የተሰበሰቡ ሙስሊም አማንያን /ፎቶ - ፋይል/

ከጁምዐ ሶላት በኋላ ሰዉ ተሰብስቦ ነበር፡፡

መሠረታዊ ናቸው ያሏቸውን ሦስት ጥያቄዎች ይዘው እየተንቀሣቀሱ ያሉት ሙስሊሞች ጥያቄዎች አጥጋቢና በቂ ምላሽ አላገኙም ሲሉ አስተባባሪዎቹ እየተናገሩ ነው፡፡

የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ አቡበከር አሕመድ ሙሐመድ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ጥያቄዎቻቸው ሲጀመር አንስቶ ከክፍለ ከተማ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅሕፈት ቤት ሲቀርቡና እስካሁንም ያልተለዋወጡ መሆናቸውን ጠቁመው በተለያዩ አካላት በየወቅቱ የተለያየ ቅርፅና ይዘት ለማሰጠት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

እነዚህ ጥያቄዎቻቸው የእሥልምና አመራር አባላት በሙስሊሙ ማኅበረሰብ የተመረጡና የተወከሉ እንዲሆኑ፤ የአህባሽን አስተሳሰብ ወይም ትምህርትና ዕምነት በሕገመንግሥቱ መሠረት በነፃነት ማሠራጨት ቢቻልም አስገድዶ ለመጫን የሚደረገው ተግባር ይቁም፤ ትልቁ የሙስሊም ተቋም አወሊያ ሙስሊሙን ሊወክሉ በሚችሉ ምሁራን እና በቦርድ ይተዳደር የሚሉ መሆናቸውን አቶ አቡበከር ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም ምርጫ ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አቡበከር ምርጫው ግን አሁን “የመንግሥት አካላት ናቸው” ባሏቸው አስፈፃሚዎች እየተካሄደ እንዳለው በቀበሌ ደረጃ ሣይሆን እንደማንኛውም ሌላ ዕምነት ሁሉ በዕምነት ተቋሙ ማለትም
በየመስጊዱ መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑና ለዚሁም እየጎተጎቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ ከሙስሊሙ ጥያቄዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ሺፈራው ተክለማርያም “የኢትዮጵያ እሥልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ዕውቅና በመንሣት ሣይሆን ተቋሙ የሕዝበ-ሙስሊሙ ተቋም ስለሆነ የሕዝበ-ሙስሊሙን ጥያቄዎች ለመመለስ እጥረት አለው ተብሎ ከታሰበ በየደረጃው ያሉ የሃይማኖቱ ምሁራን፣ አባቶች፣ ወጣቶች በመመካከር አቅምን ለመፍጠር የሚንቀሣቀሱበት ነው የሚሆነው” ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም “ይህኛውን ዕምነት ነው የምትከተለው፤ ያንን ነው የምትከተለው ብሎ ማስገደድ ከሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጭ ነው፤ መንግሥታችንም፣ ድርጅታችንም የማይተገብረው፣ በሌላ በኩልም የተገለለት ዓላማ ነው፤ ስለዚህ አህባሽ ነው የሚለው አቀራረብ ሃይማኖትን በመጫን እና ሃይማኖትን በመቀየር ሂሣብ ተወስዶ ከሆነ በጋራ የምንታገለው ነው የሚሆነው፡፡ የሃይማኖትን ዕውቀት ለማዳበር የትኛውም የዕምነት ተቋማት እንደሚተገብሩት ወስዶ መቀበል አለመቀበል የዜጎች መብት ነው” ብለዋል፡፡

የሙስሊሙ ጥያቄዎች መመለሣቸውን የጠቆሙት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ይህንን የማይቀበል የአክራሪነት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG