በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዋጋ ንረትና የገንዘብ ግሽበት በኢትዮጵያ


በኢትዮጵያ የእህል ዋጋና የሌሎች ቁሳቁስ ዋጋ እያሻቀበ መሄዱ ይታወቃል።

በተለይ የአዲስ ዘመን መቀበያ በዓልን አስታክኮ የምግብና የጥራጥሬ ዋጋ ንረት ከአርባ ከመቶ በላይ መድረሱን የአገሪቱን የስታትስቲክስ ባለሥልጣናት ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና አውታር በቅርቡ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ለኑሮው ውድነት ምክንያቶቹ ምንድናቸዉ? እንዴትስ ችግሩን ማቃለል ይቻላል? ይህ ጉዳይ ባለፈው ሣምንት ማብቂያ የ"ለጥያቄዎ መልስ" ዝግጅታችን የትኩረት ማዕከል ነበር፡፡ በርካታ አድማጮች ጥያቄዎቻቸውንና አስተያየቶቻቸውን ልከውልናል።

የኢትዮጵያን መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደግፈው የሚናገሩ የንግድ ሥራ ትምህርት ያጠኑት አቶ ሄኖክ ተስፋዬ እና በኬንታኪው የመሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስና ፋይናንስ ክፍል የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ዶክተር ሰዒድ ሃሰን፣ ለአድማጮች ጥያቄ መልስ ሰጥተውናል።

የግሽበቱ ምክንያት አንድ ወጥ እንዳልሆነ፤ ዓለም አቀፍና ሃገራዊ ምክንያት ሊኖረው እንደሚችል አቶ ሄኖክ ጠቅሰዋል፡፡ "ኢህአዴግ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያስገኛቸው ብዙ የዕድገት ትሩፋቶች ቀድሞ ሥራ ለሌላቸው ሥራ ማስገኘቱ በአገሪቱ የሸማቾች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓልና እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ ያስወድዳል" ብለዋል።

በተጨማሪም የግብርናው ዘርፍ ምርት ከህዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር ተመጣጥኖ ያለማደግ፣ ነጋዴውም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ዋጋ ሊያስወድድ የመቻሉን ነገር ለዋጋው ንረት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

አቶ ሄኖክ መንግሥት በርካታ የመፍትሔ ሃሣቦችን እንደወሰደና በዚህም ምክንያት ችግሩ በመጠኑም ቢሆን መቀረፉን ተናግረዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የኬንታኪው መሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፈሰር ዶክተር ሰዒድ ደግሞ የግብርና ምርት ያለመጨመር እና የህዝብ ቁጥር ማደግ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረትና በግሽበቱም ላይ አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ጠቁመው በዚህ ጉዳይ ከአቶ ሄኖክ ተስፋዬ ጋር እንደሚስማሙ ገልፀዋል።

ሆኖም በኢትዮጵያ ግሽበት ሁለት ዋና የሚባሉ ምክንያቶች እንዳሉት ዶክተር ሰዒድ ጠቅሰው "አንደኛው፣ የእህል አቅርቦት ማነስ ወይም እጥረት ነው ብለዋል"። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሰማኒያ በመቶ ግብርና ላይ የሚመረኮዝ መሆኑን ዶ/ር ሰዒድ ጠቅሰው ገበሬው ደግሞ ከሚያመርተው አብዛኛውን ለእራሱ ምግብነት እንደሚያውል ገልፀዋል።

በሁለተኛ ደረጃ የጠቀሱት የገንዘብ ፍሰት ሲሆን በመንግሥት ሥር ላሉ የንግድ ኩባንያዎችና ለፓርቲ ድርጅቶች መንግሥት ከውጪ የሚበደረው ገንዘብ በአገሪቱ የገንዘብ ፍሰትን እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ ለዋጋው ንረትና ለገንዘቡም ግሽበት ሌሎችም በርካታ ምክንያቶችን ዘርዝረዋል።

ሁለቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ስለኢትዮጵያ የገንዘብ ግሽበት በተለይ ደግሞ የምግብ ፍጆታ ዋጋ መናር ለአድማጮቻችን ጥያቄዎች የሰጡትን ሰፊ መልስና የመፍትሔም ሃሳብ ከዝርዝር ዘገባው ያዳምጡ።

ጥያቄ ቢኖራችሁ ወይም የራሣችሁን አስተያየት መስጠት ብትፈልጉ በemail: horn@voanews.com ወይም በስልክ ቁጥራችን 202-205-9942 አድርሱን፡፡

XS
SM
MD
LG